የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-1 ወልቂጤ ከተማ

ባህር ዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዮን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለ እንቅስቃሴያቸው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። ለእኔ ሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ወጥተናል ብዬ አስባለው። ያው ጌታነህ ሞክሮ ጌታነህ ካገባው ጎል ውጭ እኛ ላይ ብዙ ችግር አልተፈጠረብንም። በተጫለ መጠን እነርሱ ሳጥን ውስጥ ደርሰን ለማጥቃት ሞክረናል። በሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ አጨዋወት የጨዋታውን ቅርፅ እና ታክቲክ ቀይረን ለማጥቃት ሞክረን ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተናል። ሌሎች ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን አምክነናል። እኔ የማየው በቡድኔ ላይ ጥሩ መሻሻሸል አይቻለው። ከተመራን በኃላ አቻ መሆን ችለናል። ከመመራትም ማሸነፍ እንደሚቻል በልጆቼ ላይ ጥሩ ስነ ልቦና አይቻለው። በአጠቃላይ ጨዋታው ለኔ ጥሩ ነበር።

ዛሬ ላጡት ውጤት የባለፈው ጨዋታ ተፅዕኖ ስለመኖሩ

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ያደረገነውን ጥረት ዛሬም ቀጥለን ነው ያደረግነው። በእግርኳስ አንዳንዴ ጥሩ ሆነህ ነጥብ ይዘህ ሳትወጣ ትቀራለህ። ለዚህም ይህንን በፀጋ ተቀብለህ በቀጣይ ውጤት ይዘህ ያልወጣህበትን መንገድ ፈትሾ መዘጋጀት ነው የሚያዋጣው።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ያው እንደተመለከታቹሁት ነው። አርባ አምሰት ደቂቃ በልጠን አርባ አምስት ደቂቃ ብልጫ ተዎስዶብን ነበር። ቀድመን ጎል ማስቆጠር ችለን ነበር። የማይሆን ሰዓት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠብን ያሰብነውን አጨዋወት ይዘን መጫወት አልቻልንም።

ስለ ቡድኑ አጥቅቶ መጫወት

እንግዲህ ቡድናችን እንደሚታየው አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ነው። ብዙም የምንፈራው ነገር የለም። በአራት ሦስት ሦስት አጥቂ ጨምረን አስደሳች ጨዋታ ነው የምንጫወተው። ወደፊት በሄድክ ቁጥር ደጋፊው ተመልካቹ ደስተኛ ነው የሚሆነው። አሁንም ይህን አጠናክረን ነው የምንሰራው ቶሎ ቶሎ አጥቅተን እንጫወታለን። ብዙ ነገር ይቀረናል በእረፍት ጊዜያችን አስተካክለን እንመለሳለን።

ሦስት ነጥብ እስካሁን አለማሳካት

ከወልቂጤ ከተማ ዘንድሮ ብዙ ነገር ጠብቁ ብዙ ነገር ታያላቹሁ። ከና የተቀመጠ ሃያ ሰባት ጨዋታ አለ። ገና መጀመሩ ነው። ብዙ የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግንም። አስተካክለን በቀጣይ ጥሩ ነገር ይዘን እንመጣለን።