ሪፖርት | ፋሲል በሦስተኛ ተከታታይ ድል ወደ ሰንጠረዡ አናት መጥቷል

በምሽቱ ጨዋታ ቻምፒዮኖቹ ጅማ አባ ጅፋርን 4-0 በመርታት ዘንድሮም ኮስታራ ተፎካካሪ መሆናቸው አውጀዋል።

ፋሲል ከነማ በሁለተኛው ሳምንት ጉዳት የገጠማቸው ሱራፌል ዳኛቸው እና ሰዒድ ሀሰንን በአምሳሉ ጥላሁን እና አብዱልከሪም መሐመድ በመለወጥ ጨዋታውን ጀምሯል። ከጅማ አባ ጅፋር በኩል ደግሞ ከመጨረሻው ጨዋታ ታምራት ዳኜ በዮሐንስ በዛብህ ፣ አሳህሪ አልማዲ በሮጀር ማላ ፣ ሱራፌል አወል በአስናቀ ሞገስ እንዲሁም እዮብ አለማየሁ በሽመልስ ተገኝ ተተክተዋል።

ተመሳሳይ ቅርፅ እና የተቃረነ የጨዋታ አቀራረብ ይዘው ወደ ሜድ የገቡት ሁለቱ ቡድኖች ጠንከር ያለ ፉክክር በማድረግ ጀምረዋል። ኳስ ይዘው መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች ከሜዳቸው ለመውጣት ብዙ ችግር ባይገጥማቸውም ቅብብሎቻቸው ወደ ሳጥን ውስጥ ሰርገው እየገቡ አልነበረም። ከፈጣን ጥቃት መልስ በቶሎ የመከላከል ቅርፃቸውን ይይዙ የነበሩት ጅማዎች ይህ እንዳይሆን በጥንቃቄ ክፍተቶችን ሲደፍኑ ተመልክተናል። ወደ ቀኝ ያደሉት የፋሲል ጥቃቶችም ወደ ሜዳው የመጨረሻ አንድ ሦስተኛ ሲጠጉ ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች የታጀቡ ነበሩ።


በዚህ አኳኋን 6ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከግራ ያሻማው ኳስ በፍቃዱ ዓለሙ የተገጨበት እና 13ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ከቀኝ ከአብዱልከሪም መሀመድ የደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ዞሮ በመምታት የሞከረበት የተሻሉ ሙከራዎች ሆነው ቢታዩም ዮሐንስ በዛብህን ሲፈትኑ አልታየም። 19ኛው ደቂቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጅማ ጋር ወደ ሜዳ የገባው ሮጀር ማላ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በመልሶ ማጥቃት ግብ አፋፍ ለመድረስ ሲጥሩ ከነበሩት አባ ጅፋሮች በኩል የታየ ሙከራ ነበር።

30ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ጥቃት ጅማዎች ወደ መከላከል ከመሻገራቸው በፊት ቀድሞ ሳጥን ውስጥ የዘለቀበት አጋጣሚ ተከስቷል። ኳስ ይዞ የነበረው ከግራ ወደ ቀኝ መስመር የዞረው በረከት ደስታ በአስናቀ ሞገስ በመገፋቱ ፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ያሬድ ባየህ ወደ ግብነት ለውጦታል። 34ኛው ደቂቃ ላይ ጅማዎች በፍጥነት አቻ ለመሆን ተንቀሳቅሰው የአስናቀ ሞገስ ቅጣት ምት ተሻምቶ በየአብስራ ሙሉጌታ ቢገጭም ሚኬል ሳማኬ ብዙ ሳይቸገር አድኖታል።

ከግቡ በኋላው ጨዋታው ከቀደመው በተሻለ ክፍት ሆኗል። ጅማዎች ደፈር ብለው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ ታይቷል። የጅማ የማጥቃት ሙከራ በተሻለ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ሊገባ የተቃረበበት የ40ኛ ደቂቃ ቅፅበት ዱላ ሙላቱ ላይ በተሰራ ጥፋት ተቋርጧል ፤ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ የተመታው የበላይ አባይነህ ቅጣት ምትም ስኬታማ አልሆነም። በጅማ ወደፊት መግፋት ለፋሲሎች ክፍተቶችን ሲፈጥር በዛብህ እና ፍቃዱ በተሻለ ሁኔታ 42ኛው ላይ ወደ ግብ ክልል ደርሰው ጥረታቸው በሙከራ ሳይታጀብ ሲቀር ከአፍታ በኋላ በሌላ ጥቃት በዛብህ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ጉዳት የገጠመው መስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝን በቤካም አብደላ ለውጠው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ጅማዎች በጥሩ የማጥቃት ንቃት ተመልሰዋል። ቡድኑ በተሻለ አስፈሪ ቅፅበቶችን ከፈጠረባቸው አጋስታሙዎች ውስጥ 55ኛው ደቂቃ ላይ ከተስፋዬ መላኩ ወደ ሳጥን የተላከው አደገኛ የአየር ኳስ በመሐመድኑር ናስር ለመገጨት ተቃርቦ የነበረበት አንዱ ነው። የጅማዎች ደጋግሞ ወደ ፊት መሄድ ለፋሲሎች የመልሶ ማጥቃት ምልክት ሲሰጥ ቆይቶ 61ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስከትሏል። በግራ በኩል የተነሳው የበረከት ኳስ በፍቃዱ ተገጨቶ በግብ ጠባቂ ሲመለስ በዛብህ መለዮ ፈጥኖ በመድረስ ግብ አድርጎታል።

በጥሩ የማጥቃት ምልልስ በቀጠለው ጨዋት 68ኛው ደቃቃ ላይ በተከታታይ ከዱላ ሙላቱ ቀጥሎም ከፍቃዱ ዓለሙ በፈጣን ጥቃቶች ከመስመር ወደ ግብ ኳሶች ሲላኩ አይተናል። የዱላ በሳማኬ ሲይያዝ የፍቃዱ በበረከት ግብ ለመሆን ተቃርቦ ለጥቂት ወጥቷል።

በሁለቱም በኩል ግብ ጠባቂዎችን ባላስጨነቁ ግን ደግሞ አደገኛ መልክ በነበራቸው ሙከራዎች የቀጠለው ጨዋታ 79ኛው ደቂቃ ላይ ለፋሲል ሌላ ግብ አስገኝቷል። የበዛብህ እና በረከት ጥምረት በድጋሚ ሲታይ በረከት ከበዛብህ የተቀበለውን ኳስ በሳሳው የጅማ የቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ውጪ ሲያመቻችለት በዛብህ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል። ሸመክት ጉግሳ ከግቡ በኋላ ሌላ አደገኛ ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ሞክሮ ዮሐንስ በዛብህ አድኖታል።

የፋሲሎች ፈጣን ጥቃት ከሦስተኛው ግብ በኋላም አልበረደም። በዚሁ የፋሲል የግራ መስመር የበረከት ደስታ አስደናቂ የዕለቱ ብቃት ከአምሳሉ ጥላሁን ጋር የተቀናጀበት የ84ኛ ደቂቃ ኳስ ተቀይሮ ለገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የፈጠረው ዕድል በወጣቱ አጥቂ ወደ አራተኛ ግብነት ተቀይሯል። በቀሩት ደቂቃዎችም ልዩነቱን ለማጥበብ ከመሞከር ያልቦዘኑት ጅማዎች ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ለመጣል ሞክረዋል። ጥረታቸው በግብ ሳይታጀብም ጨዋታው በፋሲል ከነማ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ ያሳካው ፋሲል ከነማ ወደ ሰንጠረዡ አናት ከፍ ሲል ጅማ አባ ጅፋር ነጥብ ለማስመዝገብ ቀጣይ ጨዋታዎችን ለመጠበቅ ተገዷል።