የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 4-0 ጅማ አባ ጅፋር

ፋሲል ከነማዎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በጅማ አባ ጅፋር ላይ ካሳኩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

በሦስቱ ጨዋታዎች የቡድኑ ጥንካሬ

ትልቁ ነገር ከቡድኑ ጋር ሦስተኛ ዓመቴ ነው። ብዙ ትኩረት የምናደርገው የቡድን ሥራ ላይ ነው። በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እንደ ቡድን ካልተጫወትክ ጥቅም የለውም። በዛሬው ዕለት አራት ቋሚ ተሰላፊዎች በህመም ምክንያት ሜዳ የሉም። ግን የገቡት ተጫዋቾች እንደ ቡድን ስለሚጫወቱ የተሻለ ድምቀት እያመጣን ሄደናል። ከሁሉም በላይ ከጨዋታ ጨዋታ እያሸነፍን ስንመጣ ይህ አቋም እየጨመረ እንደሚመጣ ዕምነት አለኝ። እንደገናም ለሻምፒዮን የምንጫወት በመሆኑ እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ መቶ ፐንሰርት ትኩረት አድርገን መሄድ አለብን። ግቦች የምናገባው በውስን ተጫዋቾች አይደለም። የተለያዩ አማራጮች እናገኛለን። ይህ ሁሉ ነገሮች የቡድናችንን ጥንካሬ እያጎላው መጥቷል።

የመስመር ማጥቃታቸው በበረከት በኩል ውጤታማ ስለመሆኑ

በረከት ዘንድሮ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ አቅሙ እያደገ ነው የሄደው። ልጁ አቅም አለው፤ ከአዳማ ስናመጣው ይሄን አቅሙን አውቀን ነው። ነገር ግን ባለፉት ውድድሮች ትንሽ ወረድ ያሉ ነበር። አሁን ግን በጣም እየተነሳ ነው። እያንዳንዱ እርሱ በሚይዛቸው እንቅስቃሴዎች ላይ የቡድኑ ኃይል ይጨምራል። ይህም በራሱ ላይ በራስ መተማመኑ እየጨመረ መጥቷል፤ እንደ ቡድን መጫወት ጀምሯል። የሚያደርገውን ያውቃል፤ ቶሎ ቶሎ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንደቡድን እየጎላ መጥቷል። እነዚህ ነገሮች ተደማምረው የተሻለ ነገር እያሳየ የመጣ ይመስለኛል።

የዕረፍት ጊዜው ከእንቅስቃሴ ያወጣዋል?

የዕረፍት ጊዜው በጣም ይጠቅመናል። አንደኛ ጉዳት ላይ ያሉ ልጆች አገግመው እንዲመጡ እድል አላቸው። ሁለተኛ ልምምድ በራሱ ጫና ነው። ስለዚህ ከልምምድ ወደ ውድድር ውድድር ራሱ ጫና ነው። በእነዚህ መካከል የአንድ ሳምንት ዕረፍት ያገኛሉ። ከዛም ወደ ልምምድ የምንመለስ ስለሆነ ከእንቅስቃሴ የሚወጡ አይመስለኝም።

የጨዋታው ኮከብ

እንደምታየው በረከት ብዙ ጊዜ ጥሩ ነው። እነ በዛብህም እንደምታያቸው ናቸው። በረከት ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

በተደጋጋሚ ተረጋጉ ስለማለታቸው

ሜዳ ውስጥ ተረጋግተው ሊጫወቱ አልቻሉም። መሀል ላይ ከፍተኛ ክፍተት አለ። እንደሚታወቀው መሐሉ ፊቱን እና ኃላውን የሚያደራጅ ነው። እዛ ቦታ ላይ አንድ መንሱድ ብቻ ነው ሲባልን የነበረው። የሚፈለገውን ሥራ በአግባቡ መስራት አንችልም። በዚህ ምክንያት ነው ተረጋጉ እያልኩ እናገር የነበረው።

ስለመረጡት የጨዋታ አቀራረብ

ቅድም እንዳልኩት ከመረጋጋት አኳያ ኳሶች እግራችን ሲገቡ ይቆራረጣሉ። ቶሎ ከሰው ሜዳ የመውጣት ችግሮች ነበሩ። ከአማካይ ወደ አጥቂዎች የሚሄዱ ኳሶች በአግባቡ አይሄዱም ። ያደግሞ ከተጫዋቾች ጥራትም ችግር የሚታዩ ናቸው። በዚህ ዙርያ ብዙ መስራት እንዳለብን ያሳያል።

ስለ ሦስቱ ጨዋታዎች

በሦስቱም ጨዋታ ነጥብ ጥለናል። ነጥብ ጥለህ ጥሩ ነው የምትልበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም። በእንቅስቃሴ የመጀመርያ ሁለቱ ጨዋታዎች ጥሩ ነበሩ። የዛሬው ግን በእንቅስቃሴም ጎል አጋጣሚዎችም በመፍጠርም በመከላከል በማጥቃትም ተረጋግቶ በመጫወትም በኩል የሚታዮ ክፍተቶች አሉ። እንግዲህ እግርኳስ ሂደት ነው። በሂደት ለማስተካከል እንሞክራለን።

እረፍቱ ያለው ጠቀሜታ

በእረፍቱ ወቅት የተጫዋች ለውጥ ለማምጣት ፈታኝ ነው። ሆኖም ባለው ነገር ስራ መስራት የውዴታ ግዴታ ነው።