በዕለተ እሁዱ ሁለተኛ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ከከፍተኛ ሊጉ አብረው ከመጡ ቡድኖች ውስጥ የሆኑት መከላከያ እና አዲስ አበባ በተለያየ የአጀማመር አፅናፍ ላይ ሆነው ይገናኛሉ። ተከታታይ የ1-0 ድሎችን በማሳካት ስድስት ነጥቦችን መስብሰብ የቻለው መከላከያ ራሱን በሰንጠረዡ አናት ካሉ ቡድኖች ተርታ ማሰለፍ ችሏል። አዲስ አበባ ከተማ ከዚህ በተለየ በሁለቱም ጨዋታዎች ውጤት ሳይቀናው ካሁኑ ከመጨረሻው ደረጃ ፈቀቅ ማለት አልቻለም። አዲስ አበባ ከነገው ጨዋታ የመጀመሪያ ነጥቡን ለማሳካት የሚያልም ሲሆን መከላከያም የያዘውን መንገድ በተጨማሪ ድል ማጠናከር ዋና አላማው ይሆናል።
አረንጋዴ እና ቀይ ለባሾቹ ከድሎቹ ባሻገር እጅግ የተዋጣላቸው እንደቡድን በመከላከሉ ረገድ ነው። እስካሁን መረቡን ያላስደፈረው ቡድኑ ከፊት አጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል በስተቀር ቀሪ ተሰላፊዎቹን በቶሎ በመከላከል ወረዳው ዙሪያ የማዋቀር ጥሩ ፍጥነት አለው። ይህም ከተጋጣሚዎቹ ፈጥኖ ወደ ሳጥን የመቅረብ ፍጥነት የተሻለ ሆኖ በመታየቱ በቀላሉ እንዳይሰበር ረድቶታል። ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ ከተማ የማጥቃት ሂደት ደካማ መሆን በነገው ጨዋታ ይበልጥ ተሻሽሎ እንዲመጣ መልዕክት የሚያስተላልፍለት ነው። ከፊት አጥቂ ምርጫው ቢኒያም ጌታቸው ውጪ የመስመር አጥቂዎች እና የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮቹ እጅግ በተሻለ ፍጥነት ግብ አፋፍ የመድረስ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። ባሳለፍነው ሳምንት እንደተመለከትነው እንደ ሙሉቀን አዲሱ ዓይነት የግል ውሳኔዎችም የቡድኑን የማጥቃት ድክመት የማሻሻል ሚናቸው ቀላል የሚባል አይደለም።
አዲስ አበባ ከተማ ከወገብ በታች ያለው አደረጃጀቱም ከተጋጣሚው አንፃር በብዙ መስተካከል የሚኖርበት ነው። በተወሰነው የጨዋታ ሂደት ላይ ያለበት የኋላ ክፍሉ የትኩረት ችግር በአርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ እጅ እንዲሰጥ ምክንያት ሲሆነው ተመልክተናል። ይህንን ድክመቱን የሜዳውን ቁመት በታታሪነት ሲሸፍኑ ለተመለከትናቸው የመከላከያ የመስመር ተጫዋቾች ካጋለጠ ጨዋታው ሊከብድበት ይችላል። መከላከያዎች ነገ ከእስካሁኖቹ ሁለቱ ጨዋታዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ሊያሳዩ መቻላቸውም ለአዲስ አበባ በተለይ ፈጣን እና የአየር ላይ ጥቃቶችን በአግባቡ የማክሸፍ ብቃት ላይ መሻሻል እንድንጠብቅ የሚያደርገን ሌላው ጉዳይ ነው።
በጨዋታው እንደ መከላከያዎቹ ሰመረ ሀፍተይ እና ግሩም ሀጎስ ዓይነት በቶሎ በመስመር በኩል ወደ ግብ የመድረስ ታታሪነቱ ያላቸው ተጫዋቾች የሚፈጥሩት የአንድ ለአንድ ግንኙነት ከፊት አጥቂው ኦኩቱ ኢማኑኤል ሁለተኛ ኳሶችን የማመቻቸት ጠንካራ ጎን ጋር ተደምሮ ለጦሩ የፊት መስመር ኃይል እንደሚሆን ይጠበቅል። በአዲስ አበባ በኩል የቡድኑ የማጥቃት አማራጭ መንገድ የሆነው ፍፁም ጥላሁን የመስመር እንቅስቃሴም ኳስን ወደ ቢኒያም ጌታቸው ለማድረስም ሆነ ወድደ ግብ ለመላክ በመሞከር ውስጥ ከመከላከያ የገናናው ረጋሳ ጋር የሚፈጥረው የአንድ ለአንድ ግንኙነት ትኩረት ሳቢ የመሆን ዕድል አለው።
በጨዋታው መከላከያ ቢኒያም በላይን በጉዳት ሲያጣ በአዲስ አበባ በኩልም ፋይሰል ሙዘሙል ፣ ነብዩ ዱላ ፣ ኤልያስ አህመድ እና ቴዎድሮስ ሀሞ ከጉዳት ዝርዝር ውስጥ አልወጡም። ለቀይ ለባሾቹ ትልቁ እጦት የሚሆነው እና ለጨዋታው የሚኖረውን የቡድን መንፈስ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ግን የዋና አሰልጣኙ እስማኤል አቡበከር በክለቡ መታገድ ነው። በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲንቀሳቀስ ከምናየው መከላከያ ጋር በሚደረግ ጨዋታ የቡድኑ በንትርኮች ውስጥ ማለፍ ሜዳ ላይ የሚኖረውን የተጫዋቾች ጥረት ተፅዕኖ ውስጥ መክተቱ የሚቀር አይመስልም። ቡድኑ ግን በነገው ጨዋታ በምክትል አሰልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።
በመዲናዎቹ ሁለት ቡድኖች መሀከል የሚደረገውን ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ2009 የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን መከላከያ ሁለቱንም ጨዋታ በ2-1 እና 1-0 ውጤቶች ማሸነፍ ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – ኢብራሂም ሁሴን – ዳዊት ማሞ
ኢማኑኤል ላሪያ – አዲሱ አቱላ
ሰመረ ሀፍተይ – ብሩክ ሰሙ – ግሩም ሀጎስ
ኦኩቱ ኢማኑኤል
አዲስ አበባ ከተማ (3-5-2)
ወንድወሰን ገረመው
ኢያሱ ለገሰ – ልመንህ ታደሰ – ሮቤል ግርማ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ዋለልኝ ገብሬ – ሙሉቀን አዲሱ – ብዙአየሁ ሰይፉ – ያሬድ ሀሰን
ቢኒያም ጌታቸው – ፍፁም ጥላሁን