ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሰበታ ከተማዎች የተሻሉ የግብ እድሎችኝ ቢያገኙም በተጫዋቾቻው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሸገር ደርቢ አራት ለአንድ የተረቱበት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው የተቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ሲያስቀጥሉ በመከላከያ የተረቱት ሰበታዎች ደግሞ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል በዚህም ወልደአማኑኤል ጌቱ፣ ዘካሪያስ ፍቅሬ እና በበሃይሉ ግርማ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ በማስገባት ጨዋታቸውን አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ ከኳስ ጋር ጊዜ ባሳለፉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች ገና ጨዋታው በተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ቡናው ሮቤል ተክለሚካኤል ጫና ውስጥ ሆኖ ያቀበለውን ያልተመጠነ ኳስ አቤል ማሞ እና የግቡ አግዳሚ ተጋግዘው መለሷት እንጂ ሰበታዎች ቀዳሚ ለመሆን ቀርበው ነበር።

በጨዋታ እንቅስቃሴ የግብ እድሎችን ለማስመልከት የተቸገረው ጨዋታው በ27ኛው ደቂቃ ሮቤል ተክለሚካኤል ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ የሞከረው እና ለዓለም ብርሃኑ ያዳነበት ኳስ የአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።

ምንም እንኳን በተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢወሰድባቸውም ሰበታ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ተደጋጋሚ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በተጫዋቾቻቸው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር የተሻለ የተነቃቃ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተመልተናል ፤ በአጋማሹም ጁንያስ ናንጂቡ እና አቡበከር ናስር ባልተጠቀሙባቸው የግብ አጋጣሚዎች ጅማሮውን አድርጓል።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ሰበታዎች ፍፁም ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በተጫዋቾቻቸው ደካማ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በተለይም ጁንያስ ናንጂቡ እና ዘካርያስ ፍቅሬ በድምሩ አራት አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

በጨዋታው የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ አበበ ጥላሁን ባጋጠመው ጉዳት መነሻነት በደሳለኝ ገዛኸኝ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ፤ ኢትዮጵያ ቡናም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በአዎንታዊ ቅያሬዎቹ ታግዞ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ጥረቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

 

በዚህም ውጤት መሰረት ሁለቱም ቡድኖች የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ነጥባቸውን ማሳካት ችለዋል።

ያጋሩ