ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ሸምቷል

ያልተጠበቀ ውጤት ባስመዘገበው የምሽቱ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ መከላከያን 3-0 መርታት ችሏል።

መከላከያ ከሰበታ ከተማ ድሉ ብሩክ ሰሙን በልደቱ ጌታቸው በመቀየር ወደ ሜዳ ገብቷል። በርካታ ለውጥ ያደረጉት አዲስ አበባዎች ደግሞ ከአርባምንጩ ሽንፈት ቢኒያም ጌታቸውን በሪችሞንድ አዶንጎ ፣ ዋለልኝ ገብሬን በቻርለስ ሪባኖ ፣ ሮቤል ግርማን በሳዲቅ ተማም እንዲሁም ሳሙኤል አስፈሪን በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ ተክተዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በ 45ኛው ሰከንድ ጎል ተቆጥሮበታል። የአዲስ አበባው መሀል ተከላካይ እያሱ ለገሰ ከራሱ ሳጥን ወደ መከላከያ ሳጥን በረጅሙ የላከውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በክሌመንት ቦዬ አናት ላይ ከፍ አድርጎ ማስቆጠር ችሏል። በቶሎ ግብ ለመድረስ በሁለቱም በኩል ፍላጎት የታየበት ጨዋታ በጥሩ ፉክክር ቀጥሏል። የግብ ጠባቂዎችን ብቃት የፈተኑ ባይሆኑም በተለይም በመከላከያ በኩል የተደረጉ የግብ ሙከራዎች ጥቂት አልነበሩም።

ኳስ ይዞ የመጫወት የተሻለ ትዕግስት ኖሯቸው የታዩት አዲስ አበባዎች ተረጋግተው ከሜዳ ይውጡ እንጂ የጦሩ ተጫዋቾች ሳይደራጁ ወደ ግብ መድረስ ቸግሯቸው ታይቷል። የቡድኑ የተሻለው ሙከራም 20ኛው ደቂቃ ላይ ሳድቅ ተማም ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሲሆን ወደ ውጪ የወጣ ነበር። ቡድኑ የሜዳውን አጋማሽ ከተሻገር በኋላ ኳሶችን በቀጥታ ወደ ሳጥን ማድረስን ቀላቅሎ ለመጫወት የሞከረ ሲሆን ፊት ላይ አደጋ በመፍጠሩ በኩል ግን የተቀዛቀዘ ነበር።

መከላከያዎች በበኩላቸው አዲሱ አቱላ ወደ ተሰለፈበት የቀኝ መስመር አድልተው በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት ሲጥሩ ይታይ ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ ኦኩቱ ኢማኑኤል ከዚሁ አቅጣጫ መሬት ለመሬት ያደረሰውን ኳስ ሰመረ ሀፍተይ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ አምክኖታል። ለአዲስ አበባ የኳስ ፍሰት ምላሽ የሚሰጠው የመከላከያ የማጥቃት አማራጭ በአመዛኙ በተሻጋሪ እና የቆሙ ኳሶች የታጀበ ነበር። 25ኛ እና 30ኛ ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ ከመሀል በተነስ ቅጣት ምት አዲሱ ደግሞ ከቀኝ በማሻማት ወደ ሳጥን የላኳቸው ኳሶች በኦኩቱ እና ሰመረ ተገጭተው ግብ መሆን አልቻሉም።

ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ አዲስ አበባዎች ጠንቀቅ ብለው መልሶ ማጥቃትን የመረጡ ሲመስሉ መከላከያዎች በአንፃሩ ኳስ የመያዝ እንዲሁም በረጅሙ በመላክ ሁለተኛ ኳሶችን የመጠቀም ምልክት አሳይተዋል። ሆኖም የጦሩ ሙከራዎች ከቆሙ ኳሶች መምጣት ቀጥለዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ የግሩም ሀጎስ ለግራ ማዕዘን የተጠጋ እና በቀጥታ ወደ ጎል የተላከ ኳስ በተከላካዮች ሲወጣ 43ኛው ደቂቃ ላይ የአዲሱ የማዕዘን ምት ወደ መሬት ሲወርድ በልደቱ ተሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አዲስ አበባዎች የጥንቃቄ መከላከያዎች ደግሞ ጫና የመፍጠር ምልክት ቢታይባቸውም የጦሩ ግብ ጠባቂ ስህተት ሌላ ግብ እንድናይ አድርጎናል። ሙሉቀን አዲሱን ቀይሮ የገባው ሮቤል ግርማ ወደ ግራ አድልቶ ከተገኘ ቅጣት ምት 52ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሳጥን የላከው ኳስ በክሌመንት ቦዬ ደካማ ጊዜ አጠባበቅ ታግዞ ከመረብ አርፏል። መከላከያዎች በድጋሚ ገፍተው ለመጫወት ጥረት ቢያሳዩም የአዲስ አበባዎች ፈጣን የግራ ጥቃት ልዩነቱን ይበልጥ ለማስፋት ዘጠኝ ደቂቃቆች ብቻ ፈጅቶበታል። 61ኛው ላይ የያሬድ ሀስን ከግራ የተነሳ ኳስ ሳድቅ ተማም ሞክሮ በክሌመንት ሲመለስበት ፍፁም ጥላሁን ከግቡ አፋፍ ላይ በመገኘት ግብ አድርጎታል።


ከግቡ በኋላ መከላከያዎች ሁለቴ ሳጥን ውስጥ በብዛት ደርሰው አደጋ ቢጥሉም ዳንኤል ተሾመ እና ጓደኞቹ ተረባርበው አድነዋል። አዲስ አበባዎችም ልዩነቱ ወደ ሦስት መስፋቱን ተከትሎ በተሻለ ድፍረት በመከላከያ ሜዳ ላይ መታየት አብዝተዋል። 74ኛው ደቂቃ ላይም የሁለተኛው ጎል ኮፒ ለጥቂት ወጥቷል። ከዛው ቦታ ላይ ሮቤል በድጋሚ የላከውን ተመሳሳይ ቅጣት ምት በድጋሚ የክሌመንት ስህተት ታይቶበት ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች መከላከያዎች ወደ ኦኩቱ ኢማኑኤል ኳሶችን በማድረስ የግብ ዕድሎችን ፍለጋ ታትረዋል። ረጅሙን አጥቂ ከግብ በማገድ የተጠመዱት አዲስ አበባዎች ኳስ ይዘው ለመንቀሳቀስ የሚያደርጉት ጥረት ተጨማሪ መከላከል ሆኗቸዋል። 86ኛው ደቂቃ ላይ የጦሩ መስመር ተከላካይ ገናናው ረጋሳ በእንዳለ ከበደ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ መውጣቱ የጨዋታው ሌላ ትኩረት ሳቢ ነጥብ ሆኗል። መከላከያዎች በጭማሪ ደቂቃ በግሩም ሀጎስ እና አዲሱ አቱላ ከቅጣት ምት እና ከጨዋታ ከባድ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው አዲስ አበባዎች የ3-0 ውጤቱን አስጠብቀው ወጥተዋል።

በውጤቱ መከላከያ በሰንጠረዡ አናት ፋሲል ከነማን የመቀላቀል ዕድሉን ሲያመክን አዲስ አበባ ከግርጌ በመነሳት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ያጋሩ