የአዲስ አበባ ከተማ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሦስት ነጥብ መከላከያ ላይ ካስመዘገበ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዮን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ
ዋና አሰልጣኝ አለመኖሩ ቡድኑን ለማነቃቃት ስለመጠቀማቸው
እንደዛ አልተወሰደም። ምክንያቱም ዋና አሰልጣኝ አብሮ የነበረ ስለሆነ እርሱ አለመኖሩ ቡድኑን እንደማንቂያ የሚያዝ አይደለም።
በቡድኑ ውስጥ ስለነበረው አለመረጋጋት
እውነት ነው። ክለቡ በራሱ የዲሲፒሊን ኮሚቴ አቋቁሞ እየወሰደ ነው። ያው ደግሞ በግልም በህግ የተያዘ ስለሆነ ሲያልቅ በይፋ ይነገራል።
የመጀመርያው ጎል ጨዋታውን ለመቆጣጠር ስለመጥቀሙ
እውነት ነው። ሁልጊዜ አንድ ጎል ማስቆጠር የሥነ ልቦና የበላይነት ለመውሰድ በእጅጉን ስለሚረዳን የመጀመርያው ጎል ልጆቹን በደንብ አነሳስቷቸው ወደ ሚቀጥለው ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ረድቶናል።
ቡድኑ ከጫና የመጣ ስላለመምሰሉ
በእርግጥ የእኛ ቡድን ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም ልጆቹ በክህሎት ከሌላው ቡድን ያን ያህል ያነሱ አይደሉም። ነገር ግን የጊዜ ጉዳይ ስለሆነ ያንን ጊዜ ተጠቅመን ልክ እንደ ሌላው ቡድን ተዘጋጅተን ለመቅረብ ጊዜ በማጣቱ እንጂ ልጆቹ ጥሩ ክህሎት አላቸው። ወዲፊትም እየሰራን ስንሄድ የተሻለ ቡድን ሊሆን ይችላል።
ስለ ፍፁም ጥላሁን
ፍፁም ጥላሁን በእርግጥ አምና ከእኛ ጋር የነበረ የተሻለ ጎል ሲያስቆጥር የነበረ ተጫዋች ነው። ነገሮች ከተስተካከሉለት ከዚህ በላይ የተሻለ ጎልቶ ሊወጣ የሚችል ልጅ መሆኑን እናውቃለን። ምን አልባት ሁለቱን ጨዋታ መሸነፋችን ትንሽ ተፅዕኖ ሊፈጥርበት ይችላል። ቡድኑም እየተብላላ ሊሄድ ባለመቻሉ ምክንያት ትንሽ ጎልቶ ላይወጣ ይችላል እንጂ ፍፁም ወደፊት የተሻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ተጫዋች ነው።
ድሉ ለእረፍቱ ጥሩ ዕድል ስለመሆኑ
በእርግጠኝነት ከፍተኛ የስነ ልቡና ስንቅ ይሆነናል። ያለብንን ክፍተት ደግሞ እያረምን የተሻለ ቡድን ሆነን እንደሌላው ቡድን ለመቅረብ እንሞክራለን።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞከርም የጠራ የጎል ዕድል አለመፍጠራቸው
ከመጀመርያውም የራሳችን ስህተት ነው። ንቀህ ስትገባ ዋጋ ያስከፍልሀል። ከመጀመርያው አንድ ደቂቃ ጀምሮ ነው ዋጋ የከፈልነው። ስለዚህ በጊዜ መሆኑ ጥሩ ትምህርት ይሆናሀል። ከዚህ ውጭ የምትንቀው ቡድን የለም በሌላ ስለተሸነፈ እኔም ዝም ብዬ አሸንፈዋለው ብሎ አይሰራም። በራሳችን ስህተት ዋጋ ከፍለናል እኛው ነው የተሳሳትነው ማስተካከል አለብን።
በፍጥነት ጎል መቆጠሩ በቡድኑ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ
በመጀመርያው ደቂቃ ጎል ሲገባብህ የቡድኑ አለመረጋጋት በአይምሮ ተዘናግቶ መግባት አሸንፌ እወጣለው ብሎ ማሰብ ዋጋ ከፍለናል። አዲስ አበባ ደግሞ ጥሩ ሆኖ መጣ ማሸነፍ ይገባቸዋል።
ብልጫ የተወሰዱባቸው ቦታዎች
ብልጫ አልተወሰደብንም በራሳችን ስህተት ነው። እኛ በሰጠናቸው ዕድሎች ሁለቱ ቅጣት ምት የግብጠባቂው ስህተት መዘናጋት ነው። በአንደኛው ደቂቃ ጎል ሲቆጠርብህ በአይምሮ መደናገጥ ትጀምራለህ ሁለተኛው ሲቆጠር ደግሞ የባሰ ተስፋ እየቆረጥክ ትመጣለህ። ስለዚህ መቶ በመቶ የእኛ ስህተት ነው። እነርሱ ደግሞ ስለተጠቀሙበት አሸንፈዋል። ስህተቶች ሲበዙ ሌላ ቡድን የማጥቃት መንገዱ ብዙ ይሆናል። ስለዚህ ስህተታችንን አበዛን እነርሱ ዕድሉን ተጠቀሙ። ብዙ ጥፋቶችን እየሰራን ሁለቱ ጎሎች ሲቆጠሩ ቅጣት ምቶች ናቸው። ቅጣት ምት ደግሞ በጥፋት መስራት የመጣ ነው። ብዙ ስህተት ስትሰራ ብዙ ጎሎች ይቆጠራሉ። እነኝህን አረወመን እንመጣለን።
ስለ ግብጠባቂያቸው ክሌሜንት
መብራቱ ነው ሊል ይችላል። ያም አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ትክክልም ነው። የእኛ ሀገር መብራት ከኳሱ ጋር አብሮ መሄድ አይችልም። ይከብዳል መቶ በመቶ ይህ ምክንያት መሆን ይችላል የሚለውን ግን አልወቀበለውም። የራሱም ስህተት አለበት። ከመብራቱ ጋር ግን አልተረጋጋም። ያቺ ጎል ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ስላልተረጋጋ የራሳችን መቶ በመቶ ስህተት ነው። ያንን ብዬ መደምደም እችላለው።