የሦስተኛ ሳምንት የአራተኛ ቀን የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ዓመቱን በድል ጀምረው በሁለተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በሲዳማ ቡና የተረቱት ድሬዳዋ ከተማዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት መመለስን እያለሙ ነገ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመራው የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ በእርጋታ ኳስን ይዞ ለመውጣት የሚጥር ቡድን እንደሆነ በሁለቱ ጨዋታዎች ታይቷል። ይህ ፍላጎት ቡድኑ ላይ ቢኖርም ግን ውህደቱ ጥሩ ኳስ ይዞ የሚጫወት ስብስብ ሳያስመስለው ቀርቷል። ምናልባት ይህ የቡድኑ ተጫዋቾች የውህደት ደረጃ ጨዋታ ከጨዋታ እየተሻሻለ ከመጣ ግን በዚህ ረገድ ቡድኑ የተዋጣለት ሊሆን ይችላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ድሬዳዋ ኳስ ለመያዝ ፍላጎት ቢያሳይም የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል መሐል ለመሐል ሰብሮ መግባት የሚያስችሉ የፔኔትሬሽን ኳስች እምብዛም አላሳየም። ይህ አለመሆኑ ደግሞ ቡድኑ በሁለቱ መስመሮች በኩል ብቻ የተንጠለጠለ የማጣቃት አማራጭ እንዲኖረው ያስገደደው ይመስላል።
በተለይ በተለይ ጋዲሳ መብራቴ በሚሰለፍበት ቦታ ላይ ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት ሲከተል የታየው ቡድኑ ነገም ጊዮርጊሶችን በዚሁ ጠንካራ የማጥቂያ ክፍሉ ጥቃት ይሰነዝራል ተብሎ ይጠበቃል። በተቃራኒው ግን በተለይ በሲዳማው ጨዋታ ቡድኑ በሁለቱ ሽግግሮች (ከማጥቃት ወደ መከላከል እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት) እና ከመስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን መመከት ላይ ደከም ያለ ብቃት አሳይቷል። ነገ በዚሁ መልኩ ጨዋታውን ከቀረበ ደግሞ የጊዮርጊስ ፈጣን ጥቃት ሊያገኘው ስለሚችል መጠንቀቅ አለበት። ይህንን ተከትሎም ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት ወደ ሜዳ ይዞ ሊገባም እንደሚችል ይገመታል።
በቡድኑ ውስጥ ያሲን ጀማል እና ዳንኤል ሀይሉ ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ሲሆኑ መሐመድ አብዱለጢፍ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አውዱ ናፊዩ የሥራ ፍቃዳቸውን በማግኘታቸው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ከመዲናው ውጪ የተደረገውን ሁለተኛውን የሸገር ደርቢ አሸንፈው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአሸናፊነት ለመዝለቅ ወሳኙን ጨዋታ ይጠባበቃሉ።
በሁለቱ የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት መልክ ያለው ጨዋታ ያሳየው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ እንደቡና ኳስ ይዞ ለመልሶ ማጥቃት የሚጋለጥ ዓይነት ቡድን ሳይሆን እንደሰበታ ሊጠነቀቅ የሚችል ቡድን ሊገጥመው ይችላል። ይህንን ተከትሎም ዘለግ ያለውን ጊዜ ከኳስ ጋር ማሳለፉ ስለማይቀር የማጥቃት አማራጩን ሥል አድርጎ መቅረብ ይጠበቅበታል። ይህ ደግሞ ከሰበታ ጋር ዕድል መፍጠር ከብዷቸው ማየታችን ነገም ቀላል ጨዋታ እንዳይሆን ሊያደርገው እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል። እርግጥ ፈጣን ጥቃት መሠንዘር ላይ አደገኛ ቢሆንም የመሐል ለመሐል ጥቃቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ከዚህ ውጪ አምበሉ ሀይደር ሸረፋ ዘግይቶ ሳጥን ውስጥ እየተገኘ የሚፈጥራቸው ዕድሎች ለቡድኑ ሌላ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ ነው።
የድሬዳዋን ፈጣን የመስመር ላይ ጥቃት መመከት ለጊዮርጊሶች ፈታኙ የቤት ሥራ ይመስላል። በተለይ ደግሞ ድሬዳዋዎች በዘንድሮ የውድድር ዓመት በግራ መስመር ላይ በመሰለፍ እየተጫወተ የሚገኘውን የቸርነት ጉግሳ ቦታ አነጣጥረው ወደ ሜዳ ሊገቡ ስለሚችሉ ይህ መስመር ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ይመስላል። ከምንም በላይ ደግሞ በደርቢው ጨዋታ ብዙ አዎንታዊ ጎኖችን ያሳየው ቡድኑ ነገም በዚህ መንገዱ ሊቀጥል ይችላል።
ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ ቀደም ለ18 ጊዜያት ተገናኝተዋል። ከአስራ ስምንቱ ግንኙነት ጊዮርጊስ 13ቱን ሲረታ ድሬ ደግሞ 3 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ ነጥብ ተጋርተው ወተዋል።
– በሁለቱ ቡድኖች የ18 ጊዜ ግንኙነት 44 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። እንደ ድሉ ሁሉ ፈረሰኞቹም ግብ የማስቆጠሩንም ሪከርድ በግላቸው አድርገዋል። በዚህም 31 ጎል ድሬዳዋ ላይ ሲያስቆጥሩ ብርቱካናማዎቹ ደግሞ 13 ጊዜ አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – ሚኪያስ ካሳሁን – ሄኖክ ኢሳይያስ
ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ደምሴ
አቤል ከበደ – ሙኸዲን ሙሳ – ጋዲሳ መብራቴ
አብዱራህማን ሙባረክ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ባህሩ ነጋሽ
ሄኖክ አዱኛ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቸርነት ጉግሳ
ሀይደር ሸረፋ – በረከት ወልዴ – ከነዓን ማርክነህ
ቡልቻ ሹራ – ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ – አቤል ያለው