የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በመጀመርያው አጋማሽ ተጨማሪ ደቂቃ በተቆጠሩ ጎሎች ነጥብ ተጋርተው የወጡት ድሬዳዋ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

የሚፈልጉትን ውጤት ስለማሳካታቸው

ባለፈው ጨዋታ ተሸንፈን ስለመጣን ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ባይሆን መልካም ነው። ሊጉ ላይ አሉ ከምንላቸው አንድ ሁለት ምርጥ ቡድኖች አንዱን ነው የገጠምነው እና በተሻለ መጠን ሁለተኛ ሽንፈት እንዳያጋጥመን በተቻለ መጠን ጥንቃቄዎች ለማድረግ ሞክረናል። እንዳጠቃላይ ኳስን ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል ተጋጣሚያችንም እንዳሰብነው እረጃጅም ኳስ ተጠቅሟል። ያው ወደ ማጥቃቱ ላይ ስኬታማ አልነበርንም። ምን አልባት ወደ እረፍት እየሄድን ስለሆነ በዛ ወቅት ውስጥ ተስተካክለን መምጣት አለብን። በተለይ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ስንገባ ክፍተቶች አሉብን እርሱን አስተካክለን መምጣት እንዳለብን ያሳያል።

የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ወደ ሜዳ መመለስ

በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ በተለይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በመሆናቸው ከወረቀት አለማለቅ ጋር ተያይዞ አልገቡም ነበር። ዛሬ ግን በተወሰነ መልኩ ጥሩ የሚባል ፍንጮች ታይተዋል። ነገርግን ይህን በደንብ አዳብረን ከእረፍት መልስ ስንመጣ ስል ሆነን መመጣት እንዳለብን ያሳያል። በአጠቃላይ ግን በውጤቱ አልተከፋውም።

በሦስቱ ጨዋታ መስተካከል ስላለበት ሁኔታ

በመከላከል አደረጃጀታችን ላይ መስራት ያለብን ነገር እንዳለ ያሳያሉ። ማጥቃቱ ላይ ግን ከምንም በላይ ስል መሆን አለብን። ጎል ሊገባብህ ይችላል። ነገር ግን ቶሎ ቶሎ ጎሎች ማስቆጠር መቻል አለብን እና እዛ ላይ ሰርተን እንመጣለን።

ሜዳውን በተመለከተ

ምንም ጥርጥር የለውም ሜዳውን እያያችሁት ነው። ሜዳው ልክ አይደለም። የሚታይ ነው ለመጫወት ምቹ አይደለም። ብዙ ኳስ መጫወት ለማይፈልጉ ቡድኖች ካልሆነ በስተቀር ሜዳው ምቹ አይደለም
በዚህ ሃያ ቀን ሊታሰብበት እና ተስተካክሎ ቢቆይ ለእግርኳስ ዕድገት ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ውጤቱን በተመለከተ

ውጤቱ ማሸነፍ እና መሸነፍ ጨዋታዎች ውስጥ አሉ። ጥሩ ካልተንቀሳቀስክ እና የተስተካከለ ነገር ከሌለህ ውጤቱን ልታጣው ትችላለህ። የምንፈልገውና በጨዋታው ላይ የነበረን ፍላጎት በጣም የወረደ እና የቀነሰ ስለሆነ አቅማቸውን ሙሉ ለሙሉ አውጥተው ስላላሳዩ ውጤቱ ለእነርሱ ይገባቸዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቅያሪ

የበለጠ ማጥቃት አድርገን ጎሎች ለማስቆጠር ነበር። ወደ ሶስት አራት ሙከራዎች አግኝተናል በቦታው እና ባግባቡ ስላልተገኘን ስተናቸዋልና ያንን ለማድረግ ነበር ቅያሪ ያድግነው። እስማኤም የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ያመከናቸው እና እንቅስቃሴ ስላልነበረ ለዚህ ነው ቅያሪውን ያደረግነው።

የቡድኑ ጥንካሬ እና ድክመት

መከላከል ላይ ጥሩ ነው። ማጥቃት ላይ ብዙ ነገሮች ይቀሩናል። እነዛ ነገሮች ላይ ሰርተና የተሻለ ነጥብ እና ደረጃ ለመያዝ ብዙ የቤት ስራ አለብን እነዛ ላይ ሰርተን በቀጣይ እንቀርባለን።

ስለ ሜዳው

በምንም ተዓምር በማንኛውም ሁኔታ ሜዳው ምቹ አይደለም። ለየትኛውም ቡድን የሚመጥን ጨዋታ የምታይበት አይደለም። የቢድኖችን አቋም ማየት የማይቻልበት ነወረ። እኔ ሜዳው ላይ በጣም ቅሬታ አለኝ።

ስለ ዋናው አሰልጣኝ

አዎ በቀጣይ ጨዋታ ይመጣሉ።

ያጋሩ