ሪፖርት | አዞዎቹ እና ነብሮቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በአርባምንጭ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና መካከል የተደረገው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከአዲስ አበባው ድል ባደረጋቸው ለውጦች አሸናፊ ፊዳ ፣ ማርቲን ኦኮሮ ፣ አብነት ተሾመ እና አሸናፊ ኤሊያስ ወደ ተጠባባቂነት ወርደው በምትካቸው በርናድ ኦቼንግ ፣ ሀቢብ ከማል ፣ ኤሪክ ካፒያቶ እና እንዳልካቸው መስፍን ጨዋታውን ጀምረዋል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ ሶሆሆ ሜንሳህ እና ሄኖክ አርፌጮ በመሳይ አያኖ እና እያሱ ታምሩ ምትክ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ለዓይን ማራኪ አልነበረም። ያልተሳኩ የማጥቃት ዕቅዶች እና የተቆራረጡ ቅብብሎች ሰፍነውበት የተካሄደ ሆኗል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተሻለ ኳስ ይዘው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም በመስመርም ሆነ መሀል ለመሀል የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች አደገኛ የግብ ዕድል ይዘው ሊመጡ አልቻሉም። ወደ ኋላ ቀረት ብለው በመከላከል በቶሎ ከሜዳቸው ለመውጣት የሚጥሩት አርባምንጮችም ተጋጣሚያቸውን ፊት ላይ ጫና በመፍጠር ጭምር እንደልቡ አጋማሻቸው ላይ እንዳይገባ ቢያደርጉም የእነሱም ጥቃቶች እምብዝም ነበሩ።

ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ጥቂት ሙከራዎችን ያስመለከተን ጨዋታ 18ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ከባድ ሙከራ አስተናግዷል። ለአርባምንጭ የመጀመሪያ ጨዋታዎችን ያደረጉት ኬኒያዊያን ጥምረት የጨዋታውን የመጀመሪያ አደገኛ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። መሀል ተከላካዩ በርናድ ኦቼንግ ወደ ሳጥን የጣለው ረጅም ኳስ ኤሪክ ካፓይቶን ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶት ከሳጥን ውስጥ ቢሞክርም ሶሆሆ ሜንሳህ አድኖበታል። የተመለሰውን ኳስ ፀጋዬ አበራ በድጋሚ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የኳስ መነጣጠቁ የተበራከተበት ሆኖ ሲቀጥል ቅብብሎችም መሀል ላይ ተገድበው ቀርተዋል። ወደ ማብቂያው ላይ አርባምንጮች የተሻሉ ኳሶችን ከመስመሮች ወደ ውስጥ ለማሻገር ቢሞክሩም ጠንካራ ሙከራ ሳናይ ጨዋታው ተጋምሷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሩ ግብ አስተናግዷል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ከአርባምንጭ ሜዳ የተላከው ረጅም ኳስ በተከላካዮች ሲጨረፍ ፀጋዬ አበራ ከግራ መስመር ሲያሻማው እና ሶሆሆ ሜንሳህ በአግባቡ ማራቅ ሳይችል ሲቀር ከኳስ ጋር የተገናኘው በላይ ገዛኸኝ ወደ ግብነት ለውጦታል። ከግቡ በኋላ ጨዋታው በተመሳሳይ አኳኋን ቀጥሏል። ሀዲያዎች በቅብብሎች ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በአርባምንጮች እየተቋረጠ ተመልክተናል። 59ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገው ቀጣይ ሙከራ ግን ግብ መሆን ችሏል። ብርሀኑ በቀለ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ በአርባ ምንጭ ተከላካዮች ሲጨረፍ ሳጥን ውስጥ የደረሰው አማካዩ ፍቅረየሱ ተወልደብርሀን ወደ ግብነት በመቀየር በድኑን አቻ አድርጓል።

ሆሳዕናዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ቀጥተኝነት በታየባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች በሁለት አጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ቢገኙም የባዬ ገዛኸኝ ሙከራዎች በአስገራሚ ሁኔታ ኢላማቸውን አልጠበቁም። በተለይም 66ኛው ደቂቃ ላይ ዑመድ ዑኩሪ ከግራ ያደረሰው ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ በመሆኑ በቀላሉ ግብ አደረገው ተብሎ የተጠበቀ ነበር።

ጨዋታው የተለየ ድምቀት ባይታይበትም ወደ መጨረሻው ክስተቶች ተበራክተውበታል። ግብ አስቆጣሪው ፍቅረየሱስ በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት 84ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበት አንዱ ነው። 86ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዑመድ ዑኩሪ የባዬ ገዛኸኝ የርቀት ቅጣት ምት በግብ ጠባቂው ሲመለስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ጥፋት ተሰርቶበት ሲቋረጥ ጥፋቱ በተሰራበት ቦታ ላይ ውዝግብ ተነስቷል። በመጨረሻ ግን አርቢትሩ በሳጥን ውጪ ነው በማለት መግቢያው ላይ ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን ቅጣቱን ባዬ መትቶ ወደ ላይ ተነስቶበታል። ፉክክሩ ጥሩ ቢሆንም አሰልቺ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ያጋሩ