ሊጉ ለቀናት ዕረፍት ከመቋረጡ በፊት በተደረገው የሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት በክለቦች ዙርያ ያተኮሩ ዓበይት ጉዳዮችን አጠናቅረናል።
👉 ብኩኑ የሰበታ ማጥቃት
ኢትዮጵያ ቡና ከሰበታ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤቱ ከመጠናቀቁ በስተጀርባ የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ጉዳይ እንጂ በጨዋታው ከፈጠሯቸው ዕድሎች አሸንፈው መውጣት በተገባቸው ነበር።
ለኢትዮጵያ ቡና ኳሱን የለቀቁት ሰበታ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በተለይም ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ለማጥቃት በቁጥር በርከት ብለው ወደ ሰበታ ከተማ ሳጥን መጠጋታቸውን ተከትሎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች ግብ ለማግኘት ጥረዋል። በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ቡናን ሊጎዱባቸው የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በተጫዋቾቻቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ የተነሳ ዕድሎች ሲባክኑ ተስተውሏል።
እርግጥ የውሳኔ አሰጣጥ ክህሎትን ልምምዶች በማሰራት እንዲሻሻሉ ማድረግ በጣም ከባድ እንደሆነ ይታመናል። ምክንያቱም መሰል የማጥቃት ሁኔታዎችን የሚመስሉ ተመሳሳይ ቅፅበቶችን በልምምድ ሜዳ ላይ መፍጠር እና ተጫዋችን ማብቃት ከባድ ነው። በዚህም አሰልጣኞች ብቸኛ ማድረግ የሚችሉት ጉዳይ ተጫዋቾች በመሰል የማጥቃት አጋጣሚዎች ተረጋግተው ውሳኔዎችን እንዲሰጡ አዕምሯዊ ሥራዎችን መስራት ብቻ ነው።
የቡድኖች የመከላከል አደረጃጀት ይበልጥ እየጠነከረ በመጣበት በዚህ ወቅት ብዙ የግብ ዕድሎችን መግኘት ከባድ እየሆነ ይገኛል። በመሆኑም ዕድሎችን በጥራት መፈፀም መቻል እና አለመቻል የጨዋታ ውጤቶችን ሲወስን ይስተዋላል። በመሆኑም ሰበታ ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻ ደቂቃዎች ያገኟቸውን ውስን ዕድሎች ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ ዋጋ ሊከፍሉ የሚችሉበት ሁኔታ ነበር። በመሆኑም እንደ ሰበታ ከተማ ዓይነት ተከላካክሎ በመጫወት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚፈልግ ቡድን የማጥቃት ስልነቱን መጨመር የማይችል ከሆነ ነገሮች ሊከብዱበት ይችላል።
👉 የአዲስ አበባ ከተማ ድል
በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት ሳይጠበቁ መከላከያ ከተማን 3-0 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።
ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በመከላከያው ግብ ጠባቂ ስህተት የመጀመሪያውን ግብ ያገኙት አዲስአበባ ከተማዎች ይህች ግብ አጠቃላዩን የጨዋታ መልክ ቀይራላችዋለች። ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት መጫወት ምርጫቸው ያደረጉት መከላከያዎች ከመጀመሪያ የጨዋታ ዕቅዳቸው ወጥተው ባለመዱት የማጥቃት ጨዋታ አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ እንዲያሳልፉ ሲገደዱ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ጥንቃቄ አክለው ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ እንዲሁ አዲስ አበባዎች በተመሳሳይ በመከላከያ ግብ ጠባቂ ታግዘው ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታውን ለመከላከያዎች እጅግ ፈታኝ ማድረግ ችለዋል። እርግጥ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ለተሸነፈ ቡድን የመጀመሪያው ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ከምንም በላይ ትኩረት የሚሰጠው ቢሆንም የቡድኑ ተጫዋቾች በዘጠናው ደቂቃ ያሳዩት አስደናቂ ተነሳሽነት እና ትጋት የሚደነቅ ነበር።
በተለይም አራቱ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ በመከላከሉ ረገድ የነበራቸው ብቃት የተለየ ነበር። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የተሻለ የማሸነፍ ንፃሬ የነበራቸው ተጫዋቾቹ አስፈላጊ በሆነባቸው አጋጣሚዎችም ኃይል ቀላቅለው በመጫወት ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዎቻቸው በማድረስ እጅግ ውጤታማ የነበረ የጨዋታ ዕለት አሳልፈዋል።
ሊጉ ለቀናት ለዕረፍት ከመቋረጡ በፊት ለቡድን መፈንስ ተስፋን የፈነጠቀ ድል ማስመዝገብ መቻሉ አጠቃላይ የሥነ ልቦና ደረጃውን ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ ማጥቃት
ላለፉት አራት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዘንድሮ ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፈው በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ጀምረዋል። በእነዚህ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ በድምሩ አራት ግቦችን ማስቆጠር ቢችልም የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ግን መፈተሽ የሚያስፈልገው ነው።
ውድድሩ ገና እየተጀመረ እንደመሆኑ አራት ግቦች በሦስት ጨዋታ መጥፎ የሚባል ባይሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወገብ በላይ ከያዛቸው ተጫዋቾች ጥራት አንፃር ሲታይ ጥሩ የሚባል አይደለም። እርግጥ ግቦችን ለማግኘት ከተጫዋቾች ጥራት ባለፈ ተጫዋቾች አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ የሚያስችል የቡድን መዋቅር መዘርጋት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
የቅዱስ ጊዮርጊስን የአጥቂ አማራጮችን ስንመለከት ከእስማኤል ኦሮ-አጎሮ በስተቀር በመስመር አጥቂነት (አማካይነት) ለመጫወት የተመቹ ተጫዋቾችን ይዟል። በቁጥርም ሆነ በጥራታቸው የላቁ የመስመር አጥቂ (አማካይ) ተጫዋቾችን የያዘው ቡድኑ የእነዚህን ተጫዋቾች አቅም አሟጦ በመጠቀም ተጠቃሚ የሚሆንበትን የማጥቃት መዋቅር ግን አሁንም ያገኘ አይመስልም።
በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግዙፉ ኦሮ-አጎሮን በመጨረሻ አጥቂነት እንዲሁም ከእሱ በስተጀርባ ደግሞ በሁለት የመስመር አማካዮች እና አንድ የአጥቂ አማካይን በማስገባት ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ተስተውሏል። ምናልባት በዚህ የጨዋታ መንገድ የሚቀጥሉ ከሆነ ይህ የተጫዋቾች አደራደር የሚና መሸጋሸግ እስከሌለ ድረስ ሁለት የመስመር አጥቂ (አማካዮችን) ብቻ በሜዳ ላይ ለመጠቀም የሚያስችል ይሆናል።
እርግጥ ከአደራደሩ በዘለለ የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ጨዋታ እንደየሁኔታው ተለዋዋጭ መሆን የሚበረታታ ቢሆንም በተወሰነ መልኩ ሜዳ ላይ የተሰለፉ ተጫዋቾችን ያማከለ የጨዋታ መንገድን መከተል ግን የተሻለ ውጤታማ እንደሚያደርግ ይታመናል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ኦሮ-አጎሮን ከሜዳ አስወጥተው በአማኑኤል ገ/ሚካኤል ከቀየሩ በኃላ ፈረሰኞቹ ከቀደሙት ደቂቃዎች በበለጠ ቀጥተኛ ሆነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። ይህም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ኳሶችን በማሸነፍ ረገድ ተቸግሮ የተመለከትን ሲሆን ይህሞ የቡድኑን ማጥቃት ይበልጥ የተዳከመ እንዲሆን ያስገደደ ነበር።
ስብስቡ አሁን ላይ ካለው የአጥቂ አማራጮች መነሻነት ይበልጥ እነዚህን ተጫዋቾች ሊይዝ በሚችል አደራደር እንዲሁም በሚዋልል እንቅስቃሴ ተጫዋቾች ከኳስ መገኛ እና ከተጋጣሚ የቦታ አያያዝ መነሻነት እየተለዋወጡ የመጨረሻ አጥቂነት ሚናን እንዲወጡ ማድረጉ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ብቸኛ ስጋት ሊሆን የሚችለውና ከተጫዋቾቹ የጨዋታ ባህሪ አንፃር አጥቂዎቹ ይበልጥ ለእንቅስቃሴው ለመቅረብ ወደ መሀል ሲሳቡ ሳጥን ውስጥ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ሳጥኑን ሊያጠቃ የሚችል ተጫዋቾች እጥረት ነው። በድሬዳዋው ጨዋታ ላይ እንደተመለከትነው ይህ ሊያጋጥም ቢችልም የተጫዋቾች ተስቦ ወደ መሀል መምጣት የተጋጣሚ የተከላካዮችን ከቦታቸው ነቅለው እንዲወጡ በማስቻል የሚሰጠው ጥቅምም ታሳቢ የሚደረግ ነው።
ሊጉ ለጥቂት ቀናቶች መቋረጡ ምናልባት ለቅዱስ ጊዮርጊሶች ይህን የማጥቃት እንቆቅልሽ ለመፍታት መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።
👉 ፋሲል የድል ረሐብ የቀዘቀዘ አይመስልም
በሊጉ አሁን ላይ እየተካፈሉ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ በፋሲል ደረጃ አብረው የቆዩ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ማግኘት ከባድ ነው። በ2011 በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ መሰረት መጣል የጀመሩት “ዐፄዎቹ” ብዙ ሳይለዋወጡ አምና የሊጉ አሸናፊ ሆነው ዘንድሮ ደግሞ ጠንካራ አጀማመር እያደረጉ ይገኛሉ።
በተቃራኒው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲልን የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር በክረምቱ አስራ ስምንት ያህል ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። አምና ከነበረው ስብስባቸው አምስት ያህል ተጫዋቾችን ብቻ ማስቀጠላቸው በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለውን ሰፊ ርቀት የሚያሳይ ሀቅ ነው። ቡድኖች በተመሳሳይ በሆነ እግርኳሳዊ አስተሳሰብ ከዓመት ዓመት መጠነኛ ጥራት ሊያሳድጉ የሚችሉ ተጫዋቾችን በመጨመር እንዲቆዩ ማድረግ በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣል። አንደኛው እና ወሳኙ ጉዳይ የቡድን ውህደት ነው።
ለቡድኖች ውጤታማነት ቁልፍ ድርሻ ያለው ውህደት እንዲሁ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም። በልምምድ ሜዳዎች ከሚሰሩ ተደጋጋሚ ሥራዎች ባለፈ በፉክክር ጨዋታዎች ላይ ይበልጥ ተጫዋቾች በዋናው መድረክ እንዲፈተኑ ብሎም የተግባቦት መጠናቸው እየጨመረ በሂደት የተብላላ ቡድንን ለመገንባት ይረዳል።
የቡድን ውህደት የሚለው ሀሳብ አንደኛው መገለጫው ተጫዋቾች አንዱ የአንዱን እንቅስቃሴ በመገንዘብ እርስ በእርሳቸው የቅብብል ምርጫዎቸውን እና በእንቅስቃስ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ቀድመው በመረዳት ውሳኔዎችን ከደመነፍስ ይልቅ አስቀድመው በሚታወቁ ሂደቶች መሰረት ተናበው እንዲጫወቱ ማስቻል ነው።
ይህንን በፋሲል ከነማ ቤት በደንብ እናስተውለዋለን። በተቃራኒው ገና በጣት የሚቆጠሩ የፉክክር ጨዋታ ያደረጉት የጅማ አባ ጅፋር ስብስብ ላይ ምልክቶቹም የሉም። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኞች የስብስብ ውህደት መጠን ምን ያህል ልዩነት እንደሚፈጥር በሚያንፀባርቅ ሁኔታ ፋሲሎች ፍፁም በላቀ ትጋት አሳምነው ማሸነፋቸውን ተመልክተናል።
👉 ጅማ ዘንድሮም የሰቀቀን ዓመት ሊያሳልፍ ይሆን?
የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ ጅማ አባ ጅፋሮች ከድሉ ማግስት ከነበረው የውድድር ዘመን አንስቶ እስከ ዘንድሮው ጅማሮ ድረስ አመርቂ የሚባል ጉዞን ማድረግ እንደተሳናቸው ቀጥለዋል። ጅማ እስካሁን ድረስ በሊጉ ምንም ነጥብ ማግኘት ሳይችል በሊጉ ግርጌ ይገኛል።
በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች የተሸነፈው ቡድኑ ከውጤት ማጣት ባለፈ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ተስፋ የሚሰጥ አልሆነም። የፊት መስመሩም እንዲሁ እጅግ ደካማ የሆነ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።
ለጥንቃቄ ቅድሚያ በሚሰጡት አሰልጣኝ የኳስ ቁጥጥር ቡድን ለመሆን አልሞ ወደ ውድድር የገባው ጅማ አባ ጅፋር በብዙ መመዘኛዎች ደካማ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የቡድን ግንባታ መሰረታዊ ከሚባሉት ቅንጣቶች አንዱ የሆነው የመከላከል ክፍሉ በበርካታ ውስንነቶች ውስጥ ሆኖ እየተጓዘ ይገኛል። ከፍተኛ የአማራጮች እጥረቶች ያሉበት የቡድኑ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ከቦታቸው ውጪ በሚጫወቱ (Make Shift) የመሀል ተከላካዮች እየተጠቀመ ይገኛል።
ይህም የሚና መሸጋሸግ የሚሰጠው ጥቅም ቢኖርም በመከላከሉ ጠጣር መሆንን ለሚፈልግ ቡድን ግን የራሱን ስጋቶች መደቀኑ አይቀርም። በተመሳሳይ የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ እንዲሁ እስካሁን ምንም ዓይነት ግብ ማስገኘት አልቻለም። ከግቦች ባሻገር እንኳን ብንመለከተው የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ረገድ ቡድኑ ደካማ ቁጥሮች ነው ያሉት።
እርግጥ ማጥቃት እና መከላከል እንዲሁም ሁለቱ ሽግግሮች ለጥቂት የቡድን ተጫዋቾች የሚተውዉ ሳይሆኑ እንደ ቡድን የሚከወኑ መሆናቸው እርግጥ ነው። በዚህ ሲመዘን የጅማ አባ ጅፋር አጠቃላይ የእስካሁኑ የቡድን ሥራ አመርቂ አይደለም። በመሆኑም በፍጥነት ነገሮችን የማያስተካክል ካልሆነ እና ሌሎች ቡድኖች ነጥቦችን መሰብሰባቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ አምናም በመጨረሻ ሰዓት በትግራይ ክለቦች በሊጉ አለመሳተፍ ተከትሎ ያስቀጠሉትን የፕሪምየር ሊግ ተሳትፏቸውን ለማስቀጠል ዘንድሮም የሰቀቀን ዓመት ሊያሳልፉ ይችላሉ።
👉 ዝቅተኛ ግምት መስጠት ዋጋ ያስከፈለው መከላከያ
ከከፍተኛ ሊግ ያደገው መከላከያ ሌላኛውን ከከፍተኛ ሊግ ያደገውን እና በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደውን አዲስአበባ ከተማን ሲገጥም ለተጋጣሚው ዝቅተኛ ግምት በመስጠት ለሽንፈት ተዳርጓል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ “ከመጀመርያውም የራሳችን ስህተት ነው። ንቀህ ስትገባ ዋጋ ያስከፍልሀል። ከመጀመርያው አንድ ደቂቃ ጀምሮ ነው ዋጋ የከፈልነው። ስለዚህ በጊዜ መሆኑ ጥሩ ትምህርት ይሆናሀል። ከዚህ ውጪ የምትንቀው ቡድን የለም በሌላ ስለተሸነፈ እኔም ዝም ብዬ አሸንፈዋለው ብሎ አይሰራም። በራሳችን ስህተት ዋጋ ከፍለናል እኛው ነው የተሳሳትነው ማስተካከል አለብን።” የሚል አስተያየትን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሰጥተዋል።
በጨዋታዎች የማሸነፍ ቅድመ ግምትን ይዞ በመግባት እና በተቃራኒው ዝቅተኛ የማሸነፍ ግምት አግኝቶ ጨዋታዎችን በማድረግ ውስጥ በተጫዋቾች አዕምሮ ዘንድ የሚፈጠረው ስሜት እጅግ የተለያየ ነው። በንፅፅር ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የሚገቡ ቡድኖች ከጫናዎች ነፃ ሆነው በጨዋታው በመሸነፍ ውስጥ የሚያጡት ነገር እንደሌለ በማመን በቻለት መጠን ከጨዋታው አውንታዊ ውጤት ይዞ ለመውጣት ጥረቶችን ያደርጋሉ። ይህን እሳቤ አንዳንድ አሰልጣኞች ተጫዋቾቻቸውን እንደማነሳሻ እና የተሻለ ተንቀሳቀሰው ውጤት በማስመዝገብ ግምቶችን ለማፋለስ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ የማትጊያ ምክንያት አድርገው ወደ ጨዋታዎች ሲቀርቡ ይስተዋላል።
በተመሳሳይ ከፍ ያለ የማሸነፍ ግምት ማግኘት በራሱ ቡድንን ጫና ውስጥ የሚከት ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ሂደት ከማሸነፍ ግምቱ ባለፈ አሰልጣኞች ተጫዋቾቻቸው በዚህ እስቤ አዕምሯቸው ሳይሰረቀ በራሳቸው መንገድ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ራሳቸውን ሆነው ጨዋታዎችን እንዲቀርቡ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከፍ ያለ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
ሁለቱ ቅድመ ጨዋታ እሳቤዎች እንዳሉ ሆነው ለተጋጣሚ ቡድን ዝቅተኛ ግምት መስጠት ደረጃ ግን አደገኛ አስተሳሰብ የለም። ከወቅታዊ ውጤቶች ሆነ ከተለያዩ መነሻ ምክንያቶች በመነሳት ለተጋጣሚ ዝቅ ያለ ግምት መስጠት ብዙ ቡድኖችን ዋጋ ሲያስከፍል ተመልክተናል።
በዚህ እሳቤ ውስጥ ተጋጣሚን ከጨዋታ መጀመር አስቀድሞ በተጫዋቾች አዕምሮ አሸንፎ መግባት እና ማሸነፍ እንደሚችሉ በማመን ውስጥ ሰፊ ልዩነቶች አሉ። የተሳሳተው አስተሳሰብ “ጨዋታዎች የሚወሰኑት በ90 ደቂቃዎች በተሻለ ዝግጅት ሜዳ ውስጥ ያለህን በመስጠት ነው ” ከሚለው መሰረታዊ እግርኳሳዊ አስተሳሰብ የተፃረረ መሆኑ በራሱ አደገኛ ያደርገዋል። በሜዳ ላይም “ንቀው” የገቡት ተጋጣሚ ያልጠበቁትን ነገሮች ማድረግ ሲጀምር የተጋጣሚ ተጫዋቾች በአዕምሮ ረገድ የተሻለ ሲነቃቁ በተቃራኒው ያለው ቡድን ደግሞ ከፍተኛ ድንጋጤ እና መረባበሽ ውስጥ ሲገባ በስተመጨረሻም ውጤት ሲያጣ እንመለከታለን።
በመሆኑም እንደ መከላከያ ያሉ ከከፍተኛ ሊግ ያደጉ ቡድኖች በየትኛውም ሁኔታ ለየትኛውም ተጋጣሚ ዝቅተኛ ግምት መስጠት ተገቢ አይደለም። እርግጥ መከላከያ ከፍ ያለ የስኬት ታሪክ እና በንፅፅር ትልቅ እና ታሪካዊ ክለብ መሆኑ እውነታ ነው። ነገር ግን አሁን ላይ በዚያ በቀደመው የውጤታማነት ሞገሱ ላይ አይገኝም። ስለሆነም ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ያሉበትን ሁኔታ መገንዘብ ተገቢ ሲሆን አለፍ ሲልም የትኛውም ቡድን ለተጋጣሚዎቹ ዕኩል ትኩረት እና ቦታ መስጠት እንደሚገባው መማር ይኖርባቸዋል።
👉 ቀና እያለ የሚገኘው ወላይታ ድቻ
የውድድር ዘመኑን በድሬንዳዋ ከተማ ተሸንፈው የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማን እና አዳማ ከተማን በማሸነፍ ቀና ያሉበትን ተከታታይ ውጤት አስመዝግበዋል።
በውድድር ዘመን የመክፈቻ ዕለት በሽንፈት መጀመር በራሱ የሚፈጥረው ከፍ ያለ የሥነልቦና ጫና መኖሩ ይታመናል። ከዚህ ሽንፈት ማግስት በፍጥነት አገግሞ ውጤታማ መሆን እጅግ ፈታኝ የቤት ስራ ነው። ነገር ግን ወላይታ ድቻዎች በዚህ ረገድ ውጤታማ መሆን ችለዋል።
እንደ ቡድን ከፍ ባለ የትጋት ደረጃ የሚከላከለው ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የእንድሪስ ሰዒድን ኳስ የማቀበል ብቃት እንዲሁም የምንይሉ ወንድሙን እና ስንታየሁ መንግሥቱን ፍጥነት በመጠቀም ተጋጣሚዎች ላይ ሳይደራጁ ጉዳት ለማድረስ ጥረት ሲያደርግ ተመልክተናል። እርግጥ በመከላከሉ ከመዋቅር አንፃር በተወሰነ መልኩ የሚጠሩ ነገሮች ቢኖሩም ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ መጫወት በሚፈልገው መንገድ ላይ ዕድገቶችን እያሳየ ይገኛል።
እነዚህ ሁለት ተከታታይ ድሎች የቡድኑን ሥነልቦና ከፍ በማድረግ ረገድ የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመሆኑም ቡድኑ በእነዚህ ድሎች መነሻነት በቀጣይ ይህን ውጤታማነት ለማስቀጠል መታተር ይኖርበታል። እንዳለመታደል ሆኖ ቡድኑ ይህን የአሸናፊነት ሥነልቦና እንዳያስቀጥል በመሀል ውድድሩ ለቀናት መቋረጡ ዕድለ ቢስ ያደርገዋል።