በሦስተኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገደው መከላከያ የተጫዋች ተገቢነት ክስ መስርቷል።
የ2014 የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በጨዋታ መሐል የሚቀየሩ ተጫዋቾችን በተመለከተ አዲስ ደንብ መውጣቱ ይታወሳል። አዲሱ ደንብ በጨዋታዎች ተጋጣሚ ክለቦች አምስት ተጫዋቾችን እንዲቀይሩ የሚፈቅድ ሲሆን ከአምስቱ ተጫዋቾች መካከል ሦስቱ በአረንጓዴ ቴሴራ (ዋና ተጫዋቾች የተመዘገቡትን) ሁለቱ ደግሞ በቢጫ ቴሴራ እና ልዩ ቴሴራ የተመዘገቡትን ተጫዋቾች ብቻ እንዲቀይሩ ደንቡ ያዛል። ይህን ተከትሎ መከላከያ ከአዲስ አበባ ከተማ ባሳለፍነው እሁድ ምሽት ባደረገው ጨዋታ ከተፈቀደው ደንብ ውጭ አምስት ተጫዋቾች በአረንጓዴ ቴሴራ (ዋና ተጫዋቾች) ቀይሮ አስገብቷል በማለት ለአወዳዳሪው አካል ክስ መስርቷል።
እንደ መከላከያ ክስ ከሆነ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ተቀይረው የገቡት የሺዋስ በለው እና ምንተስኖት ዘካርያስ “የአዲስ አበባ ከተማ ቡድን ውስጥ በአረንጓዴ ቴሴራ የሚጫወቱ ናቸው። በዚህም መሠረት ከተላለፈው ደንብ ውጭ የገቡ በመሆናቸው ተገቢው የሆነ ውሳኔ ይሰጠን” በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ስነ ሥርዓት ኮሚቴ የቀረበውን የተገቢነት ጥያቄ ከመረመረ በኃላ በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።