ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ላይ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የዚህኛው ፅሁፋችን አካል ነው።

👉 ለኢትዮጵያ ቡና የመሐል ክፍል አዲስ አማራጭ የፈጠረው ሮቤል ተክለሚካኤል

ዐምና በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ኤርትራዊው አማካይ ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ቡና ግልጋሎትን መስጠት ጀምሯል ፤ በሜዳ ላይ እያሳየ ከሚገኘው ነገር መነሻነት ለኢትዮጵያ ቡና የመሀል ክፍል አዲስ አማራጭን የፈጠረ ይመስላል።

የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነው ሮቤል በኢትዮጵያ ቡና የመሀል ሜዳ ላይ ጉልበትን (Energy) ከፍ ከማድረግ ባለፈ በመከላከሉን ሆነ ማጥቃቱን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመከወን ሲጥር ተመልክተናል። በተጨማሪነትም ተጫዋቹ በተለይ በሲዳማ ቡናው ጨዋታ እንደተመለከትነው በተደጋጋሚ ኳሶችን ከርቀት ወደ ግብ የሚሞክርበት መንገድ አሁን ኢትዮጵያ ቡና በስብስቡ ካሉት ከአማካዩች የተለየ ያደርገዋል።

በአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና የተጫዋቾች አደራደር ከብቸኛው ስድስት ቁጥር አማኑኤል ዮሐንስ ግራ እና ቀኝ ካሉት ሁለት የስምንት ቁጥር አማካዮች በአንዱ እየተጫወተ የሚገኘው ሮቤል ምንም እንኳን በስምነት ቁጥር ሚና ቢሰለፍም በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ከአማኑኤል ትይዩ እየተገኘ ኳሶችን በማቋረጥ፣ ኳሶችን በማስጀመር እና ምስረታውን በማሳለጥ ሂደት አይነተኛ ሚናን ለመወጣት ሲሞክር ይስተዋላል። በዋነኝነት ግን በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ቡናዎች ካሏቸው አማካዮች የተሻለ የመከላከል ዝግጁነት እና ብርታትን በተወሰኑ አጋጣሚዎች እየተመለከትንበት እንገኛለን።

በተመሳሳይ በሜዳው የላይኛው ክፍል እየተገኘ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ያለው ተሳትፎም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለአብነትም በሰበታው ጨዋታ ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች ለአቡበከር ናስር ያደረሰበት መንገድ እንዲሁም እራሱ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ የሞከራትን ኳስ ለተመለከተ ተጫዋቹ በማጥቃቱ ረገድም አይነተኛ ሚናን መወጣት ሊችል የሚችልበትን መንገድ መመልከት ይቻላል።

ሌላኛው በቀላሉ የማይታየው የተጫዋቹ ክህሎት ኳሶችን ከርቀት የሚሞክርበት መንገድ ነው ፤ በሲዳማው እንዲሁም በሰበታው ጨዋታ ተጫዋቹ ከሳጥን ውጭ ጠንከር ያሉ ኳሶችን ወደ ግብ ሲልክ ተመልከተናል። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ቡና ላለ በሚጫወትበት የጨዋታ መንገድ መነሻነት ወደ እራሳቸው ግብ ተሰብስበው የሚከላከሉ ቡድኖች በጨዋታ እንቅስቃሴ ማስከፈት በሚቸገርበት ወቅት ከሳጥን ውጭ ከረር ባሉ ምቶች የሚላኩ ኳሶች አንደኛው የማስከፈቻ እና ግቦችን የማግኛ መንገድ እንደመሆኑ የሮቤል ጠንካራ ምቶች በዚህ ረገድ ክፍተቶች ላለበት ቡድኑ አይነተኛ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ተቀራራቢ የሆነ የጨዋታ ባህሪ (Skill Set) ያላቸው አማካዮችን ለያዘው የካሳዬ አራጌ ቡድኑ የተለየ የጨዋታ ባህሪን የተላበሰው ሮቤል ተክለሚካኤል የቡድኑን የመሀል ሜዳ ጥምረት ሆነ ለቡድኑ አጠቃላይ የጨዋታ መንገድ በቀጣይ የሚጨምረው አንዳች ነገር ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ዕድሎችን መጠቀም የተሳናቸው ጁኒያስ ናንጄቦ፥ ዘካርያስ ፍቅሬ እና ባዬ ገዛኸኝ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ድሬዳዋ ከተማን ለቆ ወደ ሰበታ ከተማ ያመራው ናሚቢያዊው አጥቂ ጁንያስ ናንጂቡ አሁኑም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከወዲሁ እድሎችን ማምከኑን ቀጥሎበታል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በድሬዳዋ ከተማ በርከት ያሉ ጨዋታዎን በፊት አልያም በመስመር አጥቂነት በመጀመር ያደረገው ይህ አጥቂ ካገኛቸው እድሎች እጅግ በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ወደ ጎልነት መቀየር ችሏል። በድሬዳዋ ከተማ መለያም ሶስት ያክል ብቻ ግቦችን ማስቆጠሩ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው። አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካዮች ጀርባ የሚገኙ ክፍት ሜዳዎችን ለማጥቃት የተመቸው አጥቂው በአስደናቂ ፍጥነት ተጫዋቾችን አልፎ የግብ አፋፍ ላይ ከደረሰ በኋላ ግን የሚወስናቸው ውሳኔዎች አሁንም አንገቱን የሚያስደፉ እንደሆኑ ቀጥለዋል።

በአዲሱ ቡድኑም በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ካሳየው ጥሩ አቋሞ አንፃር ብዙ ቢጠበቅበትም አሁንም የመጨረሻ ውሳኔዎቹ የተስተካከሉ አለመሆናቸው በተለይ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ያመከናቸው ሁለት ያለቀላቸው አጋጣሚዎች ያስመለከቱን ነበር።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ በመጀመርያ ተሰላፊነት ወደ ሜዳ የገባው ዘካርያስ ፍቅሬ የአጨራረስ ድክመት ተስተውሎበታል። በከፍተኛ ሊግ በተደጋጋሚ ግብ አስቆጣሪነቱን ያሳየው አጥቂ ፕሪምየር ሊጉ ግር ያለው የሚመስል እንቅስቃሴን ሲያሳይ ተስተውሏል። በተለይም ቡድኑን መሪ ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚን በመጀመርያ የኳስ ንክኪው ደካማነት ምክንያት ሳይጠቀምበት የቀረበት ሁኔታ ብዙ መሻሻል እንደሚጠበቅበት ማሳያ ነበር።

በክረምቱ ባህርዳር ከተማን ለቆ አወዛጋቢ በነበረ የዝውውር ሂደት ሀዳያ ሆሳዕናን የተቀላቀለው ባዬ ገዛኸኝም እንደ ናንጆቦ ሁሉ በአስደናቂ የቦታ እና የሁኔታ ግንዛቤ ግብ ለማስቆጠር በሚያስችሉ ስፍራዎች መገኘት ቢችልም የመጨረሻ ነክኪዎቹ ግን አመርቂ አልነበሩም። በመመጀመርያው ሳምንት ግሩም ግብ በፋሲል መረብ ላይ አሳልፎ የነበረው ባዬ በትናንቱ ጨዋታ ግን መልካም የጎል አጋጣሚዎችን ሲያመክን ተስተውሏል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ እንደነበራቸው ብልጫ ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር በተገባቸው ነው፥ ነገርግን በተለይ የባዬ ውሳኔ አሰጣጦች ደካማ መሆን ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አስገድዷል።

ለአንድ አጥቂ በመሰረታዊነት ግብ ማስቆጠር ከሚችልባቸው ቦታዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ጥሩ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት በመሰረታዊነት የሚጠበቁ ክህሎቶች ናቸው። እርግጥ ሁለተኛው ክህሎት በጊዜ ሂደት ይበልጥ እየተሻሻለ የሚመጣ እንደሆነ ቢታመንም በጁንያስ እና ባዬ ደረጃ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ይህን ክህሎት ከጊዜያት በኋላ እንኳን በገቢር ለማሳየት ሲቸገሩ የመመልከታችን ጉዳይ በጣም የሚያስገርም ነው።

👉የክሌመንት ቦዬ ስህተቶች

ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ መልካም የሚባል አጀማመር በማድረግ ውድድሩን የጀመሩት መከላከያዎች በሦስተኛው ጨዋታ ያልተጠበቀ ሽንፈት በአዲስአበባ ከተማ ሲያስተናግዱ ለቡድኑ ሽንፈት ተወቃሽ ከሚደረጉ ተጫዋቾች የግብ ዘቡ ክሌመንት ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።

ምንም እንኳን በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች መከላከያ ግብ ሳይቆጠርበት ይውጣ እንጂ ግብጠባቂው በተለይ ከጊዜ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየሰራ እንደነበር የምናስታውሰው ጉዳይ ነበር። ታድያ ይሄው ነገር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍል ተመልክተናል።

የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ግብ ጠባቂው የተከላካዮቹን እና የተጋጣሚን አጥቂ እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ግቡን ለቆ በመውጣቱ የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር በሁለተኛው አጋማሽም እንዲሁ የሮቤል ግርማ ግብ ሲቆጠር በተመሳሳይ የግብ መስመሩን ለቆ ለግቡ መቆጠር ምክንያት ሲሆን በተመሳሳይ ሦስተኛው ግብ በተቆጠረበት መንገድ ኳሱን የተፋበት መንገድ እንዲሁ በተወሰነ መልኩ ጥያቄ የሚነሳበት ነበር።

በዚህ መጠን አይሁን እንጂ የግብ ጠባቂው ሰሞነኛ ብቃት ግን ይህ ነገር እየመጣ እንደነበር ምልክቶችን የሚሰጥ ነበር ፤ በመሆኑም በቀጣይ ጨዋታ አሰልጣኙ ተጫዋቹ ላይ ያላቸውን እምነት አፅንተው ያሰልፉት ይሆን ወይስ ጃፋር ደሊል (ሙሴ ገ/ኪዳን) የመሰለፍ እድል ያገኛሉ ወይ የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው።

ከዚህ ቀደም በደደቢት መለያ የምናውቀው ይህ ግብ ጠባቂ ዘንድሮ ወደ መከላከያ ከመጣ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን በምልክት በመሳደብ ያልተገባ ድርጊትም ፈፅሞ እንደነበርም አይዘነጋም።

👉 ተስፈኛው ፍፁም ጥላሁን

ወጣቱ አጥቂ ፍፁም ጥላሁን ለፕሪምየር ሊግ እግርኳስ አዲስ አይደለም። ወጣቶችን በድፍረት በመጠቀም የሚታወቁት ፈረንሳዊው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ዋና ቡድን አሳድገው የመጫወት እድል ከሰጧቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ፍፁም ጥላሁን ከ2011 በኋላ ግን በፕሪሚየር ሊጉ አልተመለከትነውም ነበር።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አዲስአበባ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ አይነተኛ ሚናን የተወጣው ወጣቱ አጥቂ አሁን ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ቡድኑ ነጥብ ለማስመዝገብ ግብ አስቆጣሪ በሚፈልግበት በዚሁ ወቅት ወጣቱ አጥቂ ምላሽ ይዞ ብቅ ብሏል።

በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ምንም እንኳን ቡድኑ ቢሸነፍም በሦስት አጥቂ በጀመረባቸው አጋጣሚዎች እሱ የተሰለፈበት የቡድኑ ወገን በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ ሙከራዎችን የሚያደርገው መስመር እንደነበር ያስተዋልን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ይበልጥ ወደፊት በተጠጋ አቋቋም በጀመረበት ጨዋታ አደገኝነቱ በግቡ ያጀበበትን ምሽት አሳልፏል።

መከላከያን ሲረቱ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አጥቂው በተለይ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር አካባቢውን በፍጥነት የቃኘበት እና ውሳኔ ያሳለፈበት መንገድ በጣም የሚደነቅ ነው። ፈጣን እንዲሁም ታታሪ የሆነው አጥቂው አሁን ላይ አዲስ አበባ ከተማ በስብስባቸው ከያዛቸው አጥቂዎች የተሻለው ስለመሆኑ መመስከር ይቻላል ፤ ታድያ ይህ አጥቂ ቡድኑ በሊጉ ላለመውረድ በሚያደርገው ጥረት ምን ያክል ያግዘዋል የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ጊዜያት የሚታይ ቢሆንም መልካም የሚባሉ ፍንጮችን ሰጥቷል።

በፕሪምየር ሊጋችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርከት ያሉ ወጣት አጥቂዎች በከፍተኛ ደረጃ ሀላፊነቶችን ወስደው የክለቦችን የፊት መስመር እየመሩ ይገኛል። ይህም በጣም የሚበረታታ ተግባር ሲሆን በሌሎችም የሜዳ ክፍሎች ሆነ በሌሎች የእግርኳስ የሙያ መስኮች ላይ እንዲሁ በወጣቶች ላይ እምነት ተጥሎ ቢሰራ ምን ያህል ማትረፍ እንደሚቻል ማሳያ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ይህ አስተሳሰብ ሊዳብር ይገባል።

ፍፁም ጥላሁንን የተመለከተም ሁሉም ጨዋታዎች በሦስት አጥቂ ሲጫወቱ እሱ ያለበት መስመር ይበልጥ የጥቃት ማዕከል ይሆን ነበር። አሁን ደግሞ በ 3-5-2 ከፊት ሆኖ አደገኛነቱን በግቦች አጅቧል።

👉 የሚገባውን ያክል ክብር ያልተሰጠው በዛብህ መለዮ

ወላይታ ድቻን ለቆ ወደ ፋሲል ከነማ ካመራበት ከ2011 የውድድር ዘመን አንስቶ ቡድኑን በተመሳሳይ የብቃት ደረጃ እያገለገሉ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ተጫዋቹ ያለውን እየሰጠ እንኳን ብዙም የአድናቆት ቃላት ሲቸሩት አናደምጥም።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ምንም እንኳን በመጀመሪያው ጨዋታ ተቀይሮ የገባበት ቢሆንም በቋሚነት በጀመረባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ድንቅ እንቅስቃሴ ከማድረግ ባለፈ ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

ከግቦቹ መቆጠር በስተጀርባ ግቦቹ ያስቆጠረባቸው መንገዶች በራሱ የተጫዋቾቹን ድንቅነት የሚያሳዩ ናቸው። ከጨዋታ ሚና አንፃር ከጥልቀት የሚነሳ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው በዛብህ በጥልቀት በመነሳት ኳሶችን ከማደራጀት እና ከማሰራጨት ባለፈ ከመሀል ሜዳ እየተነሳ ዘግይቶ ወደ ሳጥኑ በመድረስ ፋሲል ከነማ የተጋጣሚ ሳጥንን በቁጥር በርከት ብሎ ለማጥቃት በሚያደርገው ጥረት አይነተኛ ሚናን ይወጣል። ከዛም ባለፈ ሳጥን ውስጥ በመገኘት ኳሶችን የሚጨርስበት መንገድም እንዲሁ የተለየ ያደርገዋል።

ከጥልቀት የሚነሱ እና ተጋጣሚ ሳጥን በመገኘት ግቦችን የሚያስቆጥሩ ብዙም አማካዮች በሌሉበት ሊጋችን እንደ በዛብህ ያሉ ይህን መወጣት የሚችሉ አማካዮች እንቅስቃሴ ለብዙዎች መማሪያ መሆን የሚችል ነው።

👉 እየተነቃቃ የሚገኘው በረከት ደስታ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብቅ የሚሉ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች ተሰጥኦን (Potential) በሙሉ ደረጃ አውጥተው በማሳየት ብቃታቸውን ሲያሳድጉ ለመመልከት ብዙም አልታደልንም። ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ ከፍ ብለው ጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ሲንሸራተቱ በሂደትም ወደ መካከለኛ ተጫዋችነት ሲወርዱ እንመለከታለን።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ተጫዋች የነበረው ተጫዋቹ ፈጣን እድገትን በማሳየት በአዳማ ከተማ አሁን ደግሞ በፋሲል ከነማ እየተጫወተ ይገኛል። በረከት ምንም እንኳን ፈጣን እድገት ቢያሳይም የብቃት ደረጃው ግን በሚፈለገው ደረጃ አድጓል ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ይልቁንም አቋሙ ወጣ ገባ የሚል አይነት ተጫዋች ሆኖም ተመልክተነዋል።

ዘንድሮ ግን ይህን ነገር ለማሻሻል ቆርጦ የተነሳ ነው የሚመስለው ተጫዋቹ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ሆነ በእስካሁኖቹ የሊግ ጨዋታዎች እያስመለከተን የሚገኘው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን በጣም አስደናቂ ነው።

ለአብነትም በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ቡድኑ ጅማ አባጅፋርን 4-0 ሲረታ በረከት ደስታ ከአራቱም ግቦች በስተጀርባ ቁልፍ ሚናን ተወጥቷል። የፋሲል ከነማ ማጥቃት አይሎ በተመለከትንበት እና በረከት ደስታ ከሚገኝበት የግራ መስመር መነሻቸውን ያደረጉት አራቱም ግቦች በረከት ደስታ ስላሳለፈው የጨዋታ ቀን በቂ ማረጋገጫ ናቸው።

በመሆኑም ተጫዋቹ አሁን የሚገኝበትን የብቃት ደረጃን ማስቀጠል የሚችል ከሆነ በቀጣዮቹ ጊዜያት የተሻለ ጊዜያትን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የዑመድ ኡኩሪ የጎል ድርቅ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ አጥቂ የነበረው ኡመድ ኡኩሪ ከአመታት የግብፅ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚመልሰውን የሀዲያ ሆሳዕና ዝውውር አምና በውድድሩ አጋማሽ ቢፈፅምም እስካሁን ግን ምንም አይነት ግብ ማስቆጠር አልቻለም።

በግብፅ በተለያዩ ክለቦች መጫወት የቻለው ዑመድ በተለይ የመጨረሻዎቹ ሁለት የውድድር ዘመናት በሰሞሃ እና አስዋን ክለቦች በጉዳት እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች መቸገሩ አይዘነጋም ፤ ታድያ ውሉን አቋርጦ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ዑመድ እስካሁን ግብ አለማስቆጠሩ ከፍተኛ ጫና የፈጠረበት ይመስላል።

ጥልቀቶችን በማጥቃት እንዲሁም ከቀኝ መስመር መነሻውን በማድረግ አጥብቦ በመግባት አክርሮ በሚልካቸው ጠንካራ ምቶች የሚታወቀው ተጫዋቹ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም ግብ አልሆንል ብሎታል። በተጨማሪም ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ወደ ኋላ ተስቦ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደ ግብ ለመድረስ እና ይበልጥ በእንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ እያስተዋልን እንገኛለን።

የትኛውም አጥቂ ላይ የሚከሰተው ይህ የግብ ድርቅ በተለይ አጥቂዎቹን ከፍ ያለ ጫና ውስጥ በመክተት ውሳኔዎቻቸው እንዲበላሹም ሲያደርግ ይስተዋላል። ለዚህ ችግር መፍትሄው እረፍት እና ግብ ማስቆጠር እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ዑመድ የመጀመሪያዋን ግብ እስኪያገኝ በዚህ የአዕምሮ ሁኔታ ውስጥ ሊቆይ እንደሚችል ይገመታል።

👉የስራ ፈቃዳቸው የዘገየባቸው የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች…

ከሥራ ፈቃድ መዘግየት ጋር በተያያዘ ምክንያት ባለፉት ጨዋታዎች ቡድናቸውን ማገልገል ያልቻሉ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተሻለ ቁጥር ቡድናቸውን ሲያገለግሉ ተመልክተናል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ጋናዊው ግብጠባቂ መሀመድ ሙንታሪ ዳግም ተፈራን ተክቶ በመግባት ለሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያውን ጨዋታ ማድረግ ሲችል በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች መጠቀም ያልቻለው ድሬዳዋ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ሁሉንም የመጠቀም እድል አግኝቷል። በዚህም አውዱ ናፊዩ ፣ መሐመድ አብዱለጢፍ እና ማማዱ ሲዴቤን ግልጋሎት ማግኘት ችለዋል።

👉 የዮሐንስ ሶጌቦ ስሜታዊነት

እግርኳስ የስሜት ስፖርት ቢሆንም አንዳንድ ድርጊቶችን በዚህ አባባል ተገቢ አድርጎ ማቅረብ (Justify) ማድረግ ግን ከባድ ነው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከትነው የዮሀንስ ሶጌቦ ድርጊትም የዚህ አይነት ነበር።

በሮድዋ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና የአቻነት ግቧን ያገኙባት የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ የሀዋሳ ከተማው ዮሀንስ ሶጌቦ ድርጊት ብዙ የሚያነጋግር ነበር። ፍፁም ቅጣቱ ምቱ በተሰጠበት ቅፅበት ዮሀንስ ውሳኔውን በመቃወም ፍፁም እሳት ለብሶ ለያዥ ለገላጋይ አስቸግሮ ተመልክተነዋል። ጨዋታውን በዳኝነት የመሩት በከፍተኛ ትዕግስት ሁኔታውን በቢጫ ካርድ አለፉት እንጂ በሜዳ ላይ የመቆየቱ ነገር ያበቃለት ይመስል ነበር።

እርግጥ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎች ሁሉንም ያስማማሉ ባይባሉም በዚህ ደረጃ ግን መለወጥ ለማይቻል የዳኛ ውሳኔ ምላሽ ማሳየት ተገቢ አለመሆኑን መረዳት ይገባል።

👉 ብሩክ በየነ እየተመለሰ ነው

በአሰልጣኝ አዲሴ ካሴ ይመራ በነበረው ሀዋሳ ከተማ በወቅቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ ከነበረው ወልቂጤ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በከፍተኛ ደረጃ ለመጫወት የሚያበቁ ነገሮች እንዳሉት ፍንጮችን አሳይቶ ነበር። ከጥሩ አጀማመር በኋላ በተወሰነ መልኩ የተቀዛቀዘ የውድድር ዘመን ያሳለፈው ብሩክ በየነ በቅድመ ውድድር ዘመን በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ከአምናው በተሻለ የንቃት ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል።

ተጫዋቹ የሀዋሳን የፊት መስመር አሁን በዋና አጥቂነት የመምራት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ብሎም በሊጉ ተቀዛቅዞ የጀመረ ቢመስልም ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የፊት አጥቂ ሆኖ ባሳለፈበት ጨዋታ የጨዋታው ቁልፍ ሰው ነበር። በተጨማሪም በጠዋታው የመጀመሪያውም ግብ ሀዋሳ ሲያስቆጥር ተስፋዬ በቀለን ቦታ ያሳተበት መንገድ ለመጀመሪያው ግብ መቆጠር አይነተኛ ምክንያት ነበር።

አሁን ላይ እየጎለበተ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ በትልቅ ደረጃ ቡድኑን ለመጥቀም ከፍ ባለ የዝግጅት ደረጃ ላይ የሚገኝ ይመስላል ፤ በቀጣይም ቡድኑን ወደ ውጤታማነት ይመራል ተብሎ የተጣለበትን ተስፋ እውን ማድረግ ይኖርበታል።