አዲስ አበባ ከተማ ቅጣት ላይ ያለ ተጫዋችን አሰልፏል በሚል ጥቆማ ተደርጎበታል

አዲሱ የሊጉ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ቅጣት ላይ ያለን ተጫዋች በጨዋታዎች አሰለፏል በሚል በሊጉ ክለብ ጥቆማ እንደተደረገበት ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሦስት ሳምንታት መርሐ-ግብሮችን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ካከናወነ በኋላ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ለ20 ቀናት ተቋርጧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሜዳ ውጪ ባሉ ነገሮች ስሙ እየተነሳ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ በሦስተኛ ሳምንት መከላከያን ገጥሞ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር የዓመቱን የመጀመሪያ ድል አሳክቷል። ታዲያ በዚህ ጨዋታ የህግ ጥሰት ተፈፅሟል ያለው መከላከያ ተጋጣሚው ከተፈቀደው ደንብ ውጭ አምስት ተጫዋቾች በአረንጓዴ ቴሴራ (ዋና ተጫዋቾች) ቀይሮ አስገብቷል በማለት ለአወዳዳሪው አካል ክስ መመስረቱን ከደቂቃዎች በፊት ዘግበን ነበር። አሁን ባገኘነው መረጃ መሠረት ደግሞ ክለቡ (አዲስ አበባ ከተማ) ሌላ አይነት ጥቆማ እንደደረሰበት ያመላክታል።

የተጫዋቾች ለውጥን በተያያዘ ክስ የመሰረቱት መከላከያዎች ባስገቡት ሌላ ጥቆማ በ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ከከፋ ቡና ጋር በ21/08/13 ጨዋታ ሲያደርግ በ88ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን አውስተው ተጫዋቹ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ምዕራፍ 5 አንቀጽ 35 ፊደል መ አንድ መደበኛ ጨዋታ መታገድ ሲገባው ከህግ ውጪ በዘንድሮ ዓመት የተደረጉትን ጨዋታዎች ተጫውቷል። እርግጥ ተጫዋቹ እንደተገለፀው ቡድኑ ከመከላከያ ጋር ከመጫወቱ በፊት ከባህር ዳር እና አርባምንጭ ጋር ሲፋለም ሜዳ ተሰልፎ መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን ጥቆማው ግን የመጣው ከሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በኋላ ነው። ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ጉዳዩን እያጣራ ሲሆን የዓምናው የከፍተኛ ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ኮምኒኬም ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲላክ በደብዳቤ መጠየቁን አረጋግጠናል። ኮሚቴውም ጉዳዩ ከተመረመረ በኋላም የሚያስተላልፈው ውሳኔ የሚጠበቅ ይሆናል።

ያጋሩ