ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ሆነዋል

ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ለሚደረጉት ጨዋታዎች ጥሪ ከቀረበላቸው 26 ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ስብስቡን እንደማይቀላቀሉ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ አለማለፉን ቀድሞ ቢያውቅም የምድብ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ህዳር 2 እና 5 ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ያደርጋል። ለእነዚህ ጨዋታዎች ለመዘጋጀት ለ26 ተጫዋቾች ከአራት ቀናት በፊት ጥሪ ያቀረቡት አሠልጣኙም ከፋሲል ከነማ የጠሯቸውን ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት እንደማያገኙ ታውቋል።

ስብስቡን የማይቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ተከላካዩ ያሬድ ባየህ ነው። በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ለክለቡ ፋሲል ከነማ ግልጋሎት እየሰጠ የብሽሽት ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ከሜዳ የወጣው ያሬድ ጉዳቱ በቶሎ ለጨዋታ ዝግጁ ስለማያደርገው ከስብስቡ ውጪ ለመሆን ተገዷል። ተጫዋቹ በአሁኑ ሰዓትም ለተጨማሪ ምርመራ ባህር ዳር እንደሚገኝም አረጋግጠናል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው ነው። ይህም ተጫዋች ፋሲል ከነማ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን በጉዳቱም የሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ላይ ሳይሳተፍ ቀርቶ ነበር። የሁለቱን ተጫዋቾች ጉዳት ተከትሎ አሠልጣኝ ውበቱ ለአዲስ ተጫዋቾች ጥሪ ያቀርባሉ የሚለውም ጉዳይ የሚጠበቅ ይሆናል።