አንድ ተጨማሪ ተጫዋች ከብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ውጪ ሆኗል

በዛሬው ዕለት ዝግጅቱን ከጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ አንድ ተጨማሪ ተጫዋች እንዳልተካተተ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በዓለም ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ጋና እና ዚምባብዌን የምትገጥመው ኢትዮጵያ ለተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዛሬ ንግድ ባንክ ሜዳ ላይ ዝግጅት በመጀመር ላይ ትገኛለች። ከተጠሩት ተጫዋቾች መካከል የፋሲል ከነማዎቹ ያሬድ ባየህ እና ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆናቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ አማኑኤል ገብረሚካኤል ሌላው ከቡድኑ ውጪ የሆነ ተጫዋች መሆኑ ታውቋል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች በግል ጉዳይ ምክንያት ፈቃድ ጠይቆ ከስብስቡ ውጪ የሆነ ሲሆን ዛሬ በንግድ ባንክ ሜዳ ከተገኙ 22 ተጫዋቾች ውስጥም እንዳልተገኘ በስፍራው ተገኝተን አረጋግጠናል።

ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ በሦስቱ ተጫዋቾች ምትክ አዲስ ምርጫ ያከናውናል ወይስ ባሉት ይቀጥላል የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ሆኗል።

ያጋሩ