ከቀናት በኋላ ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት ልምምድ ጀምሯል።
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ዚምባቡዌ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ ከወዲሁ መውደቁን ማረጋገጡ ይታወቃል። ቡድኑ ለዓለም ዋንጫው ባይበቃም ቀሪ የምድብ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግ ከአራት ቀናት በፊት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ መስራት ጀምሯል።
ድረ-ገፃችን ከሰዓታት በፊት ባስነበበችው ዘገባ ያሬድ ባየህ እና ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት እንዲሁም አማኑኤል ገብረሚካኤል ደግሞ በፍቃድ ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆናቸውን አመላክታለች። ከሦስቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ደግሞ በግብፁ ክለብ ኤል ጎውና እየተጫወተ የሚገኘው ሽመልስ በቀለን ሳይጨምር በዛሬው ዕለት 22 ተጫዋቾች ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።
ተጫዋቾቹ ቀለል ያለ የማፍታታት ሩጫ ካደረጉ በኋላ ከኳስ ጋር እንዲያላቅቁ የተደረገ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ በሦስት ቡድኖች ተከፋፍለው የመሐል ባልገባ ይዘት ያለው ልምምድ ሲሰሩ ነበር። ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ከቆየው ልምምድ በኋላ ደግሞ ሦስቱ የግብ ዘቦች (ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ተክለማርያም ሻንቆ እና ፍሬው ጌታሁን) ከግብ ጠባቂዎቹ አሠልጣኝ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ጋር በመሆን ተነጥለው ልምምዳቸውን ሲሰሩ ዋናው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ሁለቱ ረዳቶች ደግሞ ሌሎቹን ተጫዋቾች ከኳስ ውጪ ተጋጣሚ ላይ ጫና አሳድሮ መጫወትን መሠረት ያደረገ ስልጠና (Pressing) ሲሰጡ ነበር። በአራት መደቦች ተጫዋቾቹ ተናበው ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ፣ ወደ ግራ እና ቀኝ እንዲጓዙ የሚያደርገው ሥልጠና ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ በግማሽ ሜዳ ይሁ ጫና አሳድሮ የመጫወት እንቅስቃሴ ሲቀጥል ነበር። በተለይ ተጫዋቾቹ ኳስ ሲያጡ ተናበው ኳሱን የሚመልሱበትን መንገድ እንዲተገብሩ ሲደረግ ተመልክተናል።
በዛሬው የቡድኑ ልምምድ ላይ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ አስቻለው ታመነ መጠነኛ ህመም መሰማቱን ተከትሎ ለብቻው ተለይቶ ከህክማና ባለሙያው ሂርፓሳ ፋኖ ጋር ቀለል ያሉ ስራዎችን ሲሰራ አይተናል። ከአስቻለው በተጨማሪ አጥቂው አቡበከር ናስር ደግሞ ከአጋሮቹ ጋር ካፍታታ በኋላ ልምምዱን አቋርጦ ሲወጣ አስተውለናል።
ሁለት ሰዓት የፈጀው የቡድኑ ልምድም 6 ሰዓት ሲል ማብቂያውን አግኝቷል። ስብስቡ የፊታችን ማክሰኞ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያመራ ሲሆን እስከዛም ማረፊያውን በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በማድረግ ልምምዱን በቀን አንድ ጊዜ እየሰራ የሚቀጥል ይሆናል።