ሦስተኛው የዓበይት ጉዳዮች ጥንቅታችን የጨዋታ ሳምንቱን የአሰልጣኞች ጊዜ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።
👉 የዘርዓይ ሙሉ ውጤታማ ስልት
በ3ኛው የጨዋታ ሳምንት የመክፈቻ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን 2-1 የረታበት ጨዋታ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሲዳማ ቡናን የማጥቃት ጥንካሬ ያከሸፉበት መንገድ ውጤታማ ያደረጋቸው ነበር።
ሲዳማ ቡና በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 3-0 በረታበት ጨዋታ ሦስቱም ግቦች የተቆጠሩት ከመስመር ተከላካዮች መነሻ ባደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ነበር። ታድያ ይህን የተገነዘቡት አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ ሲዳማን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሲገጥሙ ይህን የሲዳማ ቡና የማጥቃት ምንጭ ለማድረቅ ቡድናቸው ከኳስ ውጪ በሚሆንባቸው የጨዋታ ክፍሎች የመስመር አጥቂዎቻቸው (መስፍን ታፈሰ እና ኤፍሬም አሻሞ) ይበልጥ በጥልቀት ወደራሳቸው ሜዳ እየተመለሱ የመስመር ተከላካዮቻቸውን እንዳያግዙ በማድረግ ሲንቀሳቅሱ ተመልክተናል።
ይህም መሆኑ ሁለቱ የሲዳማ ቡና የመስመር ተከላካዮች(ሰለሞን ሀብቴ እና አማኑኤል እንዳለ) በኩል ይሰነዘር የነበረው የሲዳማ ቡና ማጥቃት የተገደበ እንዲሆን እና የመስመር ጥቃታቸው ተፅዕኖ እንዲቀንስ እና የሲዳማ ቡና የማጥቃት እንቅስቃሴ በፍሬው ሰለሞን ፈጠራ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ነበሩ።
በእርግጥ መሰል ዕቅዶች በጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በትጋት ቢተገበሩም ተጫዋቾች በአዕምሮ እና በአካል እየደከሙ ሲሄዱ በታሰበው መጠን ውጤታማ ሆነው ላይዘልቁ ይችላሉ። ከዚህ አንፃር የሀዋሳ ተጫዋቾች በቶሎ የመከላከል ቅርፁን በመያዝ ጨዋታውን በጀመሩበት መንገድ መጨረሳቸው ለአሰልጣኙ ዕቅድ ስኬት ዋነኛ መሰረት ሆኗል።
የተጋጣሚን እንቅስቃሴ በተለይም ጥንካሬዎችን ማወቅ የቀጣይ የጨዋታ ዕቅድን 50% የሚሆነውን እንደሚይዝ በዘመናዊ እግርኳስ ይታመናል።አሰልጣኝ ዘርዓይም ለተጋጣሚያቸው ጠንካራ ጎን የሰጡት ጥሩ ምላሽ ይበል የሚያሰኝ ነው።
👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ጉዳይ?
ሰርቢያዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ”ወላጅ አባቴ አርፈዋል” በሚል ምክንያት ከክለቡ ከተለዩ ቀናት ተቆጥረዋል። እስካሁንም በክለቡ በኩል ስለመቀጠላቸው ይሁን ስለመመለሳቸው በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም የመቀጠላቸው ነገርግን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ሰርቢያዊው አሰልጣኝ በክረምቱ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ መንበረ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ በተለያዩ ምክንያቶች ቡድኑን በሜዳ ተገኝተው ሲመሩ አልተመለከትንም። ይሁንና አሰልጣኙ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ቡድኑን የመሩ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያሰሩ ቢሆንም ከሸገር ደርቢ በፊት ወላጅ አባቴ “አርፈዋል” በሚል ምክንያት ወደ ሀገራቸው ሰርቢያ ማቅናታቸው ይታወቃል።
ከወደ ሰርቢያ የሚገኙት አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም በነበሩበት ክለብ በተመሳሳይ ወላጅ አባቴ አርፈዋል በሚል ምክንያት ወደ ሀገራቸው ካመሩ በኋላ ከክለቡ ጋር የመለያየታቸው ጉዳይ የአሁኑ የወላጅ አባቴ አርፈዋል ሰበብ ከዚያኛው ሂደት ጋር ያመሳሰሉትም አልጠፉም።
በተመሳሳይ በቅርቡ እየወጡ የሚገኙ ሪፖርቶች አሰልጣኙ ሌላ ቡድንን በኃላፊነት ለመረከብ የሥራ ማመልከቻ እንዳስገቡ እየጠቆሙ ይገኛል። በመሆኑም የአሰልጣኙ በጊዮርጊስ የመቆየት ጉዳይ አጠራጣሪ የሆነ ይመስላል።
አሰልጣኙ ከቡድኑ ጋር የሚለያዩም ከሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተከታታይ ሁለተኛ የውድድር ዘመን በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ አሰልጣኝ እንዲቀይር መገደዱ ቡድን በድጋሚ አሁንም አሰልጣኝ ለውጡን ተከትሎ ሽግግር ውስጥ ይከተዋል። ይህም ደጋፊዎች ለመስማት የማይፈልጉት ዜና ነው።
ጊዮርጊስ አሰልጣኝ አልወጣልህ ያለው ይመስላላል። በተደጋጋሚ የአሰልጣኞች ሹም ሽር ውስጥ እንዲቀጥል የሚገደደው ክለቡ አሁንም ቢሆን አሰልጣኞችን የሚመለምልበት መንገድ በጣም የተጠና ሊሆን ይገባል። ቴክኒክ ዳይሬክተር የሌለው ቡድኑ በአመራሮች በኩል በሚደረግ ምልመላ አሰልጣኞች የሚያመጣበት መንገድ ውጤታማ እያደረገው አይገኝም። ይህን ሂደት ቆም ብሎ ሊያጤነው የሚገባበት ሰዓት ደግሞ አሁን ይመስላል።
👉 በውጤት ማጣት ውስጥም ያልተቀየረው የሙሉጌታ ምህረት እርጋታ
በዚህ ዘመን ውጤት በአንድ ጀምበር እንዲመጣ በሚጠበቅበት ወቅት ቡድኖችን ሆነ አሰልጣኞች ከውጤት አንፃር መገምገም የተለመደው አካሄድ ነው። ነገር ግን ሁኔታዎችን ከውጤት ውጪ ባሉ መንገዶች መገምገም የተሻለ ስሜትን የሚሰጠው አማራጭ ነው።
ሀዋሳ ከተማን ለቆ ሀዲያ ሆሳዕናን የተረከበው ወጣቱ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ከውጤት አንፃር ከተመለከትነው በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ማስመዝገብ የቻለው። ነገር ግን በጨዋታዎቹ ቡድኑ ያሳየው እንቅስቃሴ ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች እንዳሉት መናገር ይቻላል። ተስፋ ሰጪውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በውጤት ማጀብ ተሳነው እንጂ በሦስቱ ጨዋታዎች ያሳየው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነው።
ውድድሩ ሲጀመር በተከታታይ ከፋሲል እና ባህር ዳር ጋር ከባድ ጨዋታዎችን ያድርግ እንጂ በተለይ ከባህር ዳሩ ጨዋታ ጥሩ በመንቀሳቀስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከተሸነፈበት ከዛ ጨዋታ ቀጥሎ ደግሞ በዚህ ሳምንትም አርባምንጭን ሲገጥም እንዲሁ ጥሩ መንቀሳቀስ እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የተሻለ ሆኖ ቢታይም ከአንድ ነጥብ በላይ ማሳካት አልቻለም። ሁኔታው በሁለት ጨዋታዎች መጥፎ ጊዜ ሳያሳልፍ የፈለገውን ውጤት ካለማሳካት በላይ በአወዛጋቢ ውሳኔ የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄያቸው ሳይሳካ መቅረቱ ለቡድኑ አባላት ምሽቱን እጅግ የሚያስቆጭ ያደርገዋል። ለአሰልጣኙ ደግሞ ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኙ በቁጭት መደራረብ ስሜታዊ በመሆን አስተያየት ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም እጅግ ተረጋግተው ሁኔታውን ደጋግሞ በምስል መመልከት እንደሚኖርበት እና ዳኛው የተሻለ ዕይታ በሚሰጠው ቦታ ላይ የነበረ በመሆኑ ውሳኔውን እንደሚቀበል ተናግሯል።
በሊጋችን ዳኞች ለውጤት ማጣት ዋነኛ ምክንያት ሆነው በአሰልጣኞች የሚብጠለጠሉበት አጋጣሚ በቁጥር ቀላል አይደለም። በዚህ ደረጃ በውጤት ማጣት ውስጥ የቆዩ አሰልጣኞች ደግሞ ስሜታዊነትን የቀላቀለ ጠንካራ ሀሳብ መሰንዘራቸው የተለመደ ነው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ከዚህ ፍፁም በተለየ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መመልከታችን ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።
👉 የ1996 ኮከቦችን ያገናኘው ጨዋታ
በእግርኳስችን በተጫዋችነት ያለፉ ግለሰቦች በአሰልጣኝነት ብቅ ማለታቸው የተለመደ ነው። ውድድሩ በአሁኑ የፕሪምየር ሊግ ፎርማት መካሄድ ከጀመረበት 1990 በፊት በተጫዋችነት የሚታወቁ አሰልጣኞች አሁን ላይ በአንጋፋነት እየተጠቀሱ በአሰልጣኝነቱም ብዙ ዓመታትን እያሳለፉ ቀጥለዋል። አሁን አሁን ደግሞ ሊጉን በዘጠናዎቹ ውስጥ በተጫዋችነት ያደመቁ የቀደምሞው ተጫዋቾች ወጣት አሰልጣኞች ሆነው እየተሾሙ በማየት ላይ እንገኛለን።
ከእነዚህ አሰልጣኞች ውስጥ ቀደም ብሎ በሥልጠናው ውስጥ ከወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ጋር የምናውቀው መሳይ ተፈሪ አንዱ ነው። አሰልጣኙ ዘንድሮ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ወደ ውድድር ተመልሷል። በሌላ በኩል ከሀዋሳ ከተማ ጋር የዓምናውን የውድድር ዓመት በዋና አሰልጣኝነት የተመለከትነው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ዘንድሮ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ዓመቱን ጀምሯል።
በተጠናቀቀው የሦተኛው የጨዋታ ሳምንት የሁለቱ አሰልጣኞች እርስ በእርስ መገናኘት ግን ከቀድሞ ተጫዋችነት ፍጥጫ ያለፈ የታሪክ አጋጣሚን ፈጥሮ ታይቷል። ይህም በ1996 የውድድር ዓመት ሀዋሳ ከተማ ቻምፒዮን ሲሆን መሉጌታ ምህረት ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ማጠናቀቁ እና የያኔው የአርባምንጭ ከተማ አጥቂ መሳይ ተፈሪ ደግሞ በኮከብ ግብ አግቢነት መጨረሱ ነው። ዘንድሮ በአሰልጣኝነት የተገናኙት የ1996 ኮከቦቹ የጉብዝና ወራታቸውን ትዝታ በሚጠቅም መልኩ በአቻ ውጤት ተከባብረው ወጥተዋል የሚያስብል የ1-1 ውጤትን አስመዝግበውል።