ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በሦስተኛው ሳምንት የተከሰቱ ጉዳዮችን የተመለከተውን የመጨረሻ ፅሁፍ እነሆ!

👉ሜዳው አሁንም ተጫዋቾችን ለጉዳት መዳረጉን ቀጥሏል

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ የሳሩ ቁመት እና ሜዳው መድረቅ ጉዳይ አሁንም ለቡድኖች ጨዋታዎችን አስቸጋሪ ከማድረግ ባለፈ እንዲሁ ተጫዋቾችን ለጉዳት መዳረጉን ቀጥሏል።

ገና ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ የሜዳው ሁኔታ በርካቶችን ያነጋገረ የነበረ ጉዳይ ቢሆንም አሁን ላይ ሆነን ስንመለከተው በጨዋታ ሳምንታት መካከል ያለው የቀናት ልዩነት በራሱ ነገሮችን ለማስተካከል ከባድ አድርጎቴል። ቢያንስ በቀላሉ መሻሻል የሚችለው የሜዳው የእርጥበት መጠን ከጨዋታው በፊት እና በአጋማሾችም ሆነ ከጨዋታው በኋላ ውሃ እንዲጠጣ በማድረግ መጠነኛ መሻሻሎችን መፍጠር ቢቻልም ይህኛው አማራጭ አሁንም ድረስ ሲሞከር እያስተዋልን አንገኝም። ይህ አለመሆኑም አሁንም ተጫዋቾች ለጉዳት እየዳረገ ይገኛል።

ሊጉ በቀጣዮቹ ቀናት መቋረጡን ተከትሎ በሚኖረው የዕረፍት ጊዜ አወዳዳሪው አካል እና ሜዳውን በበላይነት የሚያስተዳድረው አካል የሜዳውን ሁኔታ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል። በተመሳሳይ በቀጣይ ውድድሩን የሚያስተናግዱ ከተማዎች ላይ የሚገኙ የመጫወቻ ሜዳዎች ካሁኑ አወዳዳሪው አካል በእኛ የእግርኳስ አውድ የተሻለ እንዲሆኑ ለማስቻል ጠንካራ የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎችን መስራት ይኖርበታል ስንል እናሳስባለን።

👉 አለባብሰው ቢያርሱ…

በእግርኳሳችን ውስጥ ስር ከሰደዱ አስተሳሰቦች አንዱ ሀሳቦችን የማስተናገድ ደካማነት ዋነኛው ሳይሆን አይቀርም። በእግርኳሱ ዙርያ ያሉ አካላት አንድ የጋራ የሚያደርጋቸው ባህሪ ለመደነቅ እንጂ ለመተቸት ዝግጁ አለመሆናቸው ነገር ነው።

ከዚህም መነሻነት በእነዚሁ አካላት ዙርያ የሚሰጡ የአድናቆት ቃላት ያልታጀሉባቸው ሀሳቦችን በጥርጣሬ መመልከት አለፍ ሲል ከአስተያየቱ ጀርባ የተደበቀ አጀንዳ እንዳለ ማሰብ የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ ይህን ሀሳብ አለማራመድ በራሱ የሚያስገርም እየሆነ መጥቷል።

ለአብነትም የጨዋታ ሳምንታ መጠናቀቃቸውን ተከትሎ በምናቀርበው ዓበይት ጉዳዮች በተሰኘው የጨዋታ ሳምንቱን የሚዳስሰው ፅሁፋችን ላይ የሚወጡ ፅሁፎችን ተከትሎ ከሚደርሱን ግብረ መልሶች ለመታዘብ እንደቻልነው ጥቂቶች የሚነሱትን ሀሳቦች በአውንታዊነት በመረዳት የሚወስዱት ወስደው የማይስማሙባቸውን ትተው ለመጓዝ ሲሞክሩ ጥቂት የማይባሉት ግን ፅሁፎቹን በአውንታዊ ሀሳብነት ለመረዳት ሲቸገሩ እና ይልቁንም እነርሱን ሆን ብሎ “ለመተቸት እና ለመግፋት ” የተፃፉ እንደሆነ በማሰብ ለፅሁፎቹ አሉታዊ ምላሽ ሲሰጡ ማስተዋላችንን ቀጥለናል።

አንዳንዶቹ የፅሁፎቹ ይዘቶች ምናልባት ግላዊ (Subjective) ምልከታ ቢሆኑም ከሁሉም ፅሁፎች በስተጀርባ ያለውን ትልቁን ምስል (Objective) ለተመለከተ ግን ሊጋችን ላይ የሚታዩ ድክመቶችን ለመቅረፍ የታለሙ ፅሁፎች ስለመሆናቸው መረዳት ይቻላል። በመሆኑም የእግርኳሱ አካላት ከዚህ በዘመን ያልተዋጀ አስተሳሰብ ተላቀው ከተቻለ ሊማሩባቸው የሚችሉ ነገሮች ካሉ መማር አልያም ደግሞ በቅንነት “እውነትን” መነሻ ተደርገው የሚቀርቡ ፅሁፎች መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል።

👉 በመለያዎች ላይ የሚሰፍሩ ስሞች ጉዳይ

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደሞከርነው በክለቦች መለያ ጀርባ ላይ የሚታተሙ የተጫዋቾች ስም ጉዳይ አሁንም የተዘነጋ ይመስላል። በመለያዎች ጀርባ ስሞች መፃፋቸው ይበል የሚያሰኝ ጉዳይ ቢሆንም በአንዳንዶቹ ላይ የምንመለከተው የሆሄያት ግድፈት ግን ‘ባልተፃፈ’ የሚያስብሉ ናቸው።

ተመሳሳይ ስሞች በተለያዩ መንገዶች ሊፃፉ መቻላቸው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በአንዳንድ ተጫዋቾች ጀርባ የምንመለከታቸው ስሞች ግን እጅግ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ የሚፃፉ ከመሆናቸው የተነሳ ትዝብት ላይ የሚጥሉ ሆነዋል።

እነዚሁ በግብር ይውጣ የተፃፉ የተጫዋቾች ስያሜዎች በቴሌቪዥን መስኮት ውድድሩን ለሚከታተሉ ሰዎች ዘንድ የሚፈጥረው አንዳች አሉታዊ ስሜት ይኖራል ብለንም እናምናለን። በመሆኑም ክለቦች ሆነ የመለያ ላይ ህትመት የሚሰሩ አካላት ስሞችን ከመፃፋቸው በፊት ልብ ሊሉት የሚገባ ጉዳይ ነው ስንል እናሳስባለን።

👉 እንደ ቡድን ስሜታዊ የመሆን ጉዳይ

በጨዋታ ወቅት በዳኞች የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ተከትሎ በቁጥር በርከት ብሎ ዳኛን መክበብ እና ማዋከብ የእግርኳሳችን አንዱ አሉታዊ መገለጫ ሆኗል።

ይህ ጉዳይ ብዙ የተባለለት ቢሆንም ሁኔታው ከመሻሻሎች ይልቅ እየተባባሰ እየመጣ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለአብነት ያህል ሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ከአርባምንጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ በዳኞች የተወሰኑ አንዳንድ ውሳኔዎችን ተከትሎ የምንመለከተው ከውሳኔው በተቃራኒ የቆሙ ተጫዋቾች ማዕበል ቀላል የሚባል አልነበረም።

ውሳኔው የተሰጠባቸው ቡድን ተጫዋቾች ከእንቅስቃሴው ቅርብ ያሉ ተጫዋቾች ውጪ ከእንቅስቃሴ ሩቅ ያሉት የቡድን አባላት ዳኛውን ለመክበብ በደህናው ጊዜ ሜዳ ላይ ከሚሮጡት የማፈትለክ ሩጫ ባልተናነሰ ፍጥነት ዳኛውን ጋር ደረሰው ሲያዋክቡ በሁለቱ ጨዋታዎች የተመለከተነው ገሀድ ሀቅ ነው።

ከዚህ የቡድን ድርጊት በተጨማሪ አንዳንድ ተጫዋቾች ደግሞ ከመስመር ባለፈ ሁኔታ የዳኞችን ትዕግስት ሲፈትኑና ብሎም በቀይ ካርድ ለመውጣት የጓጉ እስኪመስል ፍፁም ያልተገቡ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ተመልክተናል። በመሆኑ አሁንም ቢሆን ተጫዋቾቻችን ልብ ግዙ ለማለት እንወዳለን።