ኢትዮጵያዊቷ ዳኛ ወሳኙን ጨዋታ ትመራለች

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው ውድድር በነገው ዕለት የሚከናወነውን ትልቅ ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ የመሐል ዳኛ በአርቢቴርነት ትመራዋለች።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ከዘንድሮ ጀምሮ በየዓመቱ የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር እንዲከናወን መወሰኑ ይታወቃል። የየሀገራቱ የሊግ አሸናፊዎች በስድስት ዞኖች የማጣሪያ ውድድሮችን አከናውነው አሸናፊዎቹ ከዛሬ ጀምሮ በግብፅ አስተናጋጅነት በሚከናወነው ዋናው ውድድር ላይ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል። ታዲያ በዚህ ውድድር ሀገራችን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመወከል ከጫፍ ደርሳ የነበረ ቢሆንም በማጣሪያው የፍፃሜ ጨዋታ ቡድኑ በቪሂጋ ኩዊንስ ተሸንፎ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል። ይህ ቢሆንም ግን ከሀገራችን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሠ ወደ ስፍራው አቅንታለች።

አውስትራሊያ ላይ ለሚደረገው ለ2023 ዓለም ዋንጫ አካላዊ እና ተያያዥ ምዘናዎችን ለማድረግ ከሳምንት በፊት ወደ ኳታር አቅንታ የነበረችው ሊዲያ ኅዳር 21 ከኳታር ወደ ግብፅ በመግባት ከቀጣዩ ቀን (ኅዳር 22) ጀምሮ የቫር ስልጠና በግብፅ ስትከታተል ነበር። በርካታ ዳኞችን ያካተተው ስልጠና በትናንትናው ዕለት መጠናቀቁን ተከትሎ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎችን የማይመሩ ዳኞች ወደየሀገራቸው ሲጓዙ ሊዲያ ግን ጨዋታዎችን ለመምራት ቀድማ በመመረጧ እዛው ግብፅ ቆይታለች።

በስምንት ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድር ዛሬ መክፈቻውን ሲያደርግ ሊዲያ ግን በነገው ዕለት በሞሮኮው ኤፍኤአር ራባት (አርሚ ሮያል ራባት) እና በናይጄሪያው ሪቨርስ አንግልስ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ እንድትመራ ተመድባለች። በካይሮ አል-ሠላም ስታዲየም የሚደረገውን ተጠባቂ ጨዋታም ሊዲያ ከማላዊ፣ ኬንያ እና ቶጎ ከመጡ ረዳቶቿ ጋር እንደምትመራው ታውቋል።