ከፍተኛ ሊግ | ገላን ከተማ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የቀድሞው አሰልጣኙን በድጋሚ የቀጠረው የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ገላን ከተማ አስራ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾች ሲያስፈርም የነባሮቹንም ውልም አራዝሟል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ስር ከሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ገላን ከተማ የቀድሞው አሰልጣኙ ዳዊት ታደለን ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በድጋሚ መቅጠሩ ይታወሳል፡፡ በርካታ የክለቡ ነባር ተጫዋቾች ለተለያዩ ክለቦች አሳልፎ የሰጠው ቡድኑ ለ2014 የውድድር ዘመን አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በማቀፍ በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን አሰልጣኙም አስራ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ መቀላቀል ሲችሉ የአምስት ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት አራዝመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አምስት ወጣት ተጫዋቾችን ከታችኛው የክለቡ ቡድን እንዲያድጉ ተደርጓል፡፡

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ እና የኢኮሥኮ ግብ ጠባቂ አላዛር መርኔ፥ የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማ ሰበታ ከተማ እና ወልዋሎ የመስመር አጥቂ እና ተከላካይ ፍርዳወቅ ሲሳይ፥ የቀድሞው የጅማ አባጅፋር እና መከላከያ አጥቂ የነበረው ተመስገን ገብረኪዳን፥ ዓምና ወደ ኢኮስኮ በውሰት ከኢትዮጵያ ቡና አምርቶ የነበረው እና በድጋሚ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት የሦስት ዓመት ፊርማን አኑሮ የነበረው አማካዩ በየነ ባንጃውን ጨምሮ ፉአድ ነስሩ ተከላካይ ከኮልፌ ቀራኒዮ ፣ ፉአድ ጀማል ከአ.አ ፣ ዮሀንስ ዘገዬ ከኢኮስኮ ተከላካይ ፣ ይደነቁ የሺጥላ ከመድን ተከላካይ ፣ አረጋሀኝ ማሩ ከፋ ቡና አማካይ ፣ ብሩክ እንዳለ ለገጣፎ አማካይ ፣ ተሾመ መንግስቴ አቃቂ ቃሊቲ አማካይ ፣ ቴዎድሮስ ገ/እግዚአብሔር አዳማ ከነማ አማካይ ፣ ጌታለም ማሙዬ ከሻሸመኔ ከተማ አማካይ ፣ እዩኤል ሳሙኤል ከሀላባ አጥቂ ፣ ቤዛ መድህን ኢኮስኮ አጥቂ እና ቢኒያም ሁሴን ቢሾፍቱ ከተማ አጥቂ ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ፈራሚዎች ናቸው፡፡

ክለቡ ከአዲስ ፈራሚዎች ባሻገር ውብሸት ጭላሎ ግብ ጠባቂ ፣ ዓለማየው ኃይሉ ተከላካይ ፣ ታምራት ሀ/ማርያም ተከላካይ ፣ ያሬድ እሸቴ አጥቂ እና አፍቅሮት ሰለሞን አጥቂ ውላቸውን ያደሰ ሲሆን አምስት ወጣት ተጫዋቾችን ከታችኛው ቡድን ማሳደጉን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡