ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ጌዲኦ ዲላ የአሰልጣኙን ውል ሲያራዝም አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ጌዲኦ ዲላ የአሰልጣኙን ውል ሲያድስ አዳዲስ ሰባት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ክለቡ በክረምቱ በርካታ በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ነባር ተጫዋቾችን ያጣ ቢሆንም በምትኩ ግን አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ያመጣ ሲሆን ውላቸው ተጠናቆ ከነበሩ ነባር ተጫዋቾች ጋር በማድረግም በክለቡ መቀመጫ ከተማ ዲላ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ክለቡ ጀምሯል፡፡ ቡድኑ ተጫዋቾችን ከማስፈረሙ ቀደም ብሎ ክለቡን ከምስረታው ጀምሮ በማሰልጠን ላይ የሚገኘውን የአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካን ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት ያደሰ ሲሆን ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችንም በእጁ አስገብቷል፡፡

የቀድሞዋ የሙገር ሲሚንቶ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አማካይ አዲስ ንጉሴ ፣ የቀድሞዋ የአዳማ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር አጥቂ ጤናዬ ወመሴ ፣ የቀድሞ የክለቡ አጥቂ ቤተል ጢባን ከአርባምንጭ ከተማ ያስፈረመ ሲሆን በተጨማሪም መቅደስ ተሾመ (አጥቂ ከባህርዳር ከተማ)፣ ሰብለወንጌል ወዳጆ (አጥቂ ባህርዳር ከተማ)፣ አማሩ አብተው (ተከላካይ ከባህርዳር ከተማ)፣ ሣራ ብርሀኑ (ግብ ጠባቂ ከቅዱስ ጊዮርጊስ) ክለቡ የተቀላቀሉ ሲሆን ይታገሱ ተገኝወርቅ ፣ ማርያም ታደሰ ፣ መታሰቢያ ክፍሌ ፣ ሰሚራ ከድር ፣ መኪያ ከድር እና ተጨማሪ ሌሎች ስድስት በድምሩ 11 ተጫዋቾች ውላቸው ሲራዘም አምስት ወጣት ተጫዋቾችንም ክለቡ ከአካባቢው ካሉ ፕሮጀክቶች አሳደጓል፡፡