የዋልያዎቹ አማካይ አዲስ አበባ ገብቷል

በግብፁ ኤል ጎውና የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለመቀላቀል በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ገብቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ኅዳር 2 ከጋና እንዲሁም ኅዳር 5 ከዚምባቡዌ ጋር ያደርጋል። ታዲያ ለእነዚህ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ከአራት ቀናት በፊት የጀመረው ብሔራዊ ቡድኑም ያሬድ ባየህ እና ሱራፌል ዳኛቸውን በጉዳት፣ አማኑኤል ገብረሚካኤልን በግል እንዲሁም ፋሲል ገብረሚካኤልን በድንገተኛ ሀዘን ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ማድረጉ ይታወቃል። አሠልጣኙም የግብ ዘቡ ፋሲል ሲወጣ በምትኩ ጀማል ጣሰውን ጠርተዋል።

ከአራቱ ተጫዋቾች ውጪ ያሉት 22ቱ ተጫዋቾች በቀን አንድ ጊዜ ልምምዳቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ እየሰሩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ወሳኙን አማካኛቸውን ያገኛሉ። እስከ ትናንት በስትያ ድረስ ለክለቡ ኤል ጎውና ጨዋታ ሲያደርግ የነበረው ሽመልስ ለአራት ሰዓት የተጠጋ በረራ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ቦሌ ዐየር ማረፊያ እንደደረሰ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። የቡድኑ አጋሮቹ እርሱ አዲስ አበባ ሲደርስ ልምምድ ለመስራት ወደ ሜዳ መውጣታቸውን ተከትሎም ከልምምድ መልስ በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደሚቀላቀላቸው ታውቋል። ተጫዋቹ በነገው ዕለትም ልምምድ የሚጀምር መሆኑ ተመላክቷል።

ያጋሩ