ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በቅርቡ የቀድሞው አሰልጣኙን በድጋሚ ምርጫው ያደረገው አዳማ ከተማ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሟል፡፡

ለ2014 የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ ካወጣ በኋላ ሀሳቡን በመቀየር ክለቡን ከዚህ ቀደም ማሰልጠን የቻለውን አሰልጣኝ ኤፍሬም እሸቱን የቀጠረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተካፋዩ አዳማ ከተማ አሰልጣኙን ከመቅጠሩ በፊት በረዳት አሰልጣኙ አማካኝነት ፈርመው የነበሩ ተጫዋቾችን በመተው ወሳኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን በይፋ አስፈርሟል፡፡

የቀድሞዋ የደደቢት አማካይ እና አምና በመከላከያ ያሳለፈችው ኤደን ሽፈራው፣ አንጋፋዋ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ እና ዓምና በኤሌክትሪክ ያሳለፈችው ሰሚራ ከማል፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መከላከያ እና አምና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይታ የነበራት ተከላካይዋ መሰሉ አበራ፣ የቀድሞዋ የክለቡ አማካይ ዮዲት መኮንን ከሀዋሳ ከተማ፣ ደመቀች ዳልጋ ተከላካይ ከጌዲኦ ዲላ እና ትዕግስት ዘውዴ አማካይ ከአቃቂ ያስፈረመ ሲሆን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አማካይ ፅዮን ፈየራን ክለቡ ለመቀላቀል ከጫፍ መድረሱንም ሰምተናል፡፡ በተጨማሪም ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሁለት ተጨማሪ ወጣት ተጫዋቾችን በቀጣዮቹ ቀናት ይቀላቅላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ክለቡ ከወራት በፊት ከአዳዲሶቹ ባሻገር የምርቃት ፈለቀ፣ ሰርካዲስ ጉታ፣ ቅድስት ቦጋለ፣ ሄለን እሸቱ፣ ሰላማዊት ለአከ እና ፎዚያ ዝናቡ ውላቸው መታደሱም ይታወሳል፡፡

 

ያጋሩ