በድሬዳዋ ከተማ እና ኤልአውቶ መካከል የተካሄደው የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ዝርዝር

“ድሬዳዋ በራሷ አቅም በርካቶችን መሳብ ትችላለች፤ ወደፊትም ብዙዎችን መሳቧ ይቀጥላል” የከተማው ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር

“የዘመናዊ የስልጣኔ እና የኢንዱስትሪ መነሻ ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ ክለብን ስፖንሰር በማድረጋችን ደስታ ይሰማናል” የኤልአውቶ ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ አበበ


የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ከኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሬዲንግ ጋር ያደረገው የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ዛሬ በድሬዳዋ ራስ ሆቴል በተከናወነ ዝግጅት ይፋ ሆኗል።

የዕለቱ የክብር እንግዶች አቶ ከድር ጁሀር (የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ) እና አቶ በቀለ አበቤ (የኤልአውቶ ሥራ አስኪያጅ) እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙት በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሱልጣን አሊይ በንግግራቸው ” ድሬዳዋ ከተማ እግርኳስ ክለብን በአዲስ አደረጃጀት እና አሠራር ለማዘመን መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ይህንንም ለማጠናከር ከክለቡ የበላይ ጠባቂ እና የከተማው ከንቲባ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት የክለቡን አቅም ለማጠናከር የተለያዩ ስፖንሰሮች ለማምጣት ያደረገው ጥረት ተሳክቶ ከኤልአውቶ ጋር ይህን ስምምነት መፈፀማችን አስደስቶናል። ” ብለዋል።

የኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ አበበ በበኩላቸው “የዘመናዊ የስልጣኔ የኢንዱስትሪ መነሻ ከተማ የሆነችው ድሬዳዋ ከተማን እንዲሁም ቀደምት የእግርኳስ ማዕከል የሆነችውን ከተማ እግርኳስ ለማሳደግ ስፖንሰር ማድረጋችን ደስታ የተሰማን ሲሆን ለሁለት ዓመት ከሚቆየው ስምምነት በተጨማሪ በቀጣይም ከከተማዋ ጋር አብሮ የመልማት፣ የመሥራት እና የማደግ ትስስር ከዚህ በበለጠ ምዕራፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።” ካሉ በኋላ ከስፖንሰር ስምምነቱ በተጨማሪ ለዋናው ቡድኑ ተጫዋቾች ከዚህ በኃላ ጎል ለሚያገባ ተጫዋች አምስት ሺህ ብር እና በጣም ለጎል የቀረበ ኳስ ለሚያድን ግብጠባቂ በየጨዋታው ሦስት ሺህ ብር እንደሚሰጡ መግለፃቸው በዕለቱ የነበረውን ታዳሚ አስደስቷል።

ይፋዊ የስምምነት መርሐ ግብሩ በአስቂኝ ቀልዶች እና ግጥሞች እንዲሁም በማርሽ ባንድ ጥዑመ ዜማ እየተዋዛ ቀጥሎ የክለቡ የበላይ ጠባቂ እና የከተማው ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በንግግራቸው ”ድሬዳዋ ከተማ ለማኝ ቡድን አይደለም። ትልቅ አቅም ያለው ቡድን ነው።” ያሉ ሲሆን በማስከተል ”ድሬደዋ ለሀገሪቱ እግርኳስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች ያበረከተች የበርካታ ተቋማት መገኛ ከተማ ነች። ድሬዳዋ በራሷ አቅም በርካቶችን መሳብ ትችላለች፤ ወደ ፊትም ብዙዎችን መሳብ ትቀጥላለች። ይህ ስምምነት የክለቡን አቅም ከማጠናከሩ ባሻገር የታሪካዊ ከተማን ቅርሶች ባህሎችን ያቀፈ ትጥቅ መሠራቱ ልዩ ያደርገዋል። በከተማው ያሉ ሌሎች ተቋማትም ወደዚህ ተግባር እንዲገቡ መልዕክት አስተላልፋለሁ” ብለዋል።

በማስከተለት በሁለቱ አካላት መካከል የፊርማው ሥነስርዓት ከተካሄደ በኋላ ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች የሆነው ጎፈሬ በዋና ሥራ አሰኪያጁ አቶ ሳሙኤል መኮንን አማካኝነት ለከተማው ከንቲባ የከተማዋን ገፅታ የሚገልፅ ሰንደቅ ዓለማ ያበረከተ ሲሆን በተጨማሪም ለኤልአውቶ ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ አበበ የድርጅቱ ሥያሜ ያረፈበት መለያ በስጦታ አበርክተዋል። በመጨረሻም ደማቅ የነበረው የፊርማ ስነ ስርዓት የኬክ ቆረሳ ከተካሄደ በኃላ ምሽቱን ተጠናቋል።

በኤልአውቶ እና በድሬዳዋ ከተማ መካከል የስፖንሰር ሺፕ ዝርዝር ነጥቦች

– የስምምነቱ የውል ዘመን – ለሁለት ዓመት

ድሬዳዋ ከተማ በስፖንሰርሺፑ አማካኝነት የሚያገኛቸው ጥቅሞች

– 5 ሚሊዮን ብር እና 53 ሰዎች የመጫን አቅም ያለው ዘመናዊ አንድ አውቶቢስ ያገኛል።

– ለክለቡ አመራሮች የቡድን አሰልጣኞችና የተጫዋቾች የመጫወቻ የልምምድ ትጥቆችን ወጪ ይሸፍናል።

– ቡድኑ ከ1-3 ከወጣ ዳጎስ ያለ የማበረታቻ ሽልማት ይበረከትለታል።

– 3 እና 5 ተከታታይ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ የማበረታቻ ሽልማት ይሰጠዋል።

– 20 ሺህ የደጋፊዎች ማልያ ገዝቶ ትርፉን ከክለቡ ጋር እኩል ይካፈላል።

ስፖንሰር አድራጊው የሚያገኘው ጥቅሞች

– ቡድኑ የሚለብሳቸው የመጫወቻ፣ የልምምድ፣ የጉዞ እና የመግቢያ ትጥቆች ላይ የስፖንሰር አድራጊው ሁለት ብራንዶች ይተዋወቃሉ።

– 20 ሺህ የደጋፊዎች ማልያ ላይ ህትመት ላይ የስፖንሰር አድራጊው አርማ ይተዋወቃል።

– ቡድኑ ልምምድ በሚያደርግባቸው ከሜዳም ከሜዳ ውጭ ስፖንሰሩ ይተዋወቃል።

– ቡድኑን በተመለከቱ ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫ፣ ኮንሰርት፣ ባዛር እና መሠል ዝግጅቶች ወቅት የድርጅቱ አገልግሎት ይተዋወቃል።

– በዲኤስ ቲቪ በሚተላለፉ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ወቅት የሜዳ ውስጥ ማስታወቂያ ቦርድ/ባነር ይቀመጣል።

– የክለቡ ዘመናዊ አውቶብስ ላይ ስምምነት የተፈፀመባቸው የስፖንሰሩ አርማዎች ይቀመጣሉ።