በነገው ዕለት ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ረፋድ ላይ የመጨረሻ ልምምዳቸውን አዲስ አበባ ላይ ሰርተዋል።
ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ገና ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ከጉዞው መሰናከሉ ይታወሳል። ምንም እንኳን ቡድኑ ዋና ዓላማውን ባያሳካም የምድብ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ለማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ልምምዱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ እየሰራ ይገኛል።
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በቅድሚያ ከጠሯቸው 26 ተጫዋቾች ያሬድ ባየህ እና ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል በፍቃድ እንዲሁም ፋሲል ገብረሚካኤል ደግሞ በድንገተኛ የቤተሰብ ሀዘን ምክንያት፣ ዛሬ ደግሞ ሽመክት ጉግሳ በግል ጉዳይ ከስብስቡ ውጪ የሆኑ ሲሆን በግብ ዘቡ ፋሲል ምትክ ደግሞ ጀማል ጣሰው እንደ አዲስ ጥሪ ተደርጎለት እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል። በቀን አንድ ጊዜ ለሁለት ሰዓታት የቆየ ልምምዱን ሲሰራ የነበረው ቡድኑም በትላንትናው ዕለት ወሳኝ አማካዩ ሽመልስ በቀለን በማግኘት የተሟላ ልምምዱን ሰርቷል። ዛሬ ደግሞ ከ4 ሰዓት ጀምሮ በተመሳሳይ ለሁለት ሰዓት የቆየ የመጨረሻ የአዲስ አበባ ላይ ልምምዱን ሰርቷል።
ቀለል ባለ ሩጫ ተጫዋቾች እንዲያፍታቱ ከተደረገ በኋላ በሁለት ቦታ ተከፍለው እርስ በእርስ ኳስ እየተቀባበሉ እና እየገፉ እንዲያላቅቁ ተደርጓል። ለጥቂት ደቂቃዎች ከቆየው ከዚህ ልምምድ በኋላ ደግሞ ተጫዋቾች በሦስት ቦታ ተከፋፍለው በርከት ላለ ደቂቃ መሐል ባልገባ አይነት ጨዋታ እንዲጫወቱ ተደርጓል። በተለያዩ አይነቶች (በሁለት እና በአንድ ንክኪ እንዲሁም በቀማ) ከቀጠለው ልምምድ በኋላ ደግሞ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ሜዳውን ወደ ጎን ለጥጠው ወደ ጎል የሚደርሱበትን ሥልት አሠልጣኙ ሲያሰሩ የነበረ ሲሆን ከዛም ቡድኑ ለአራት ተከፍሎ አምስት አምስት በመሆን የግማሽ ሜዳ ጨዋታ አድርጓል። በመጨረሻ ደግሞ አስራ አንድ አስራ አንድ ሆነው የግማሽ ሜዳ ጨዋታ ካደረጉ በኋላ የዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር ተጠናቋል። ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ በታዘበችው መሠረት ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።
ከልምምዱ በፊት ባረፉበት ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የኮቪድ-19 ክትባት የወሰዱት የቡድኑ አባላትም ነገ ረፋድ 2:30 የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከጋና ጋር ወደሚያደርጉበት ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙ ይሆናል።