👉🏼 ”ከተጫወትናቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱ በቀትር ላይ መሆኑ ጫና ነበረው”
👉🏼 ” ከጨዋታው ከኛ ማሸነፍን ጠብቁ”
👉🏼 ”ሀገራችን ይህ ዋንጫ ያስፈልጋታል”
በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከያዝነው ወር አጋማሽ ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር በስድስት ሀገራት መካከል ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ ፍፃሜውን ያገኛል። ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ እኩል 12 ነጥብ የሰበሰቡት ኢትዮጵያ እና አዘጋጇ ሀገር ዩጋንዳም ለውድድሩ አሸናፊነት ወሳኝ ፍልሚያቸውን ዛሬ 9፡30 ላይ ያደርጋሉ።
በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጂቡቲን በማሸነፍ የጀመረውን ጉዞ በተከታታይ ድሎች ያጀበ ሲሆን የመጨረሻውን ጨዋታ በድል በማጠናቀቅ ፍፃሜውን ያሳምራል ወይ የሚለው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል። ቡድኑ ከጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ታንዛንያ እና ቡሩንዲ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በድል በመወጣት 15 አስቆጥሮ 1 ብቻ ተቆጥሮበት በአስተናጋጇ ዩጋንዳ በግብ ልዩነት ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የዛሬው ጨዋታ አሸናፊው የሚለይበት ከመሆኑ በተጨማሪ ሁለቱን ጠንካራ ቡድኖች የሚያገናኝ መሆኑም ተጠባቂ ያደርገዋል።
እንደ መጀመሪያ ተሳትፎው ብዙ ርቀት የተጓዘውን ይህንን ቡድን የሚመሩት አሠልጣኙ ውድድሩን በተመለነተ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ላለፉት 13 ቀናት በቆየው ውድድር በአጭር ቀናት ልዩነት ተደራራቢ ጨዋታዎች መከናወናቸው ለሴቶች ከባድ ቢሆንም ይህን ጫና ተቋቁመው እዚህ መድረሳቸውን ገልፀዋል። ”በተለይ በውድድሩ ላይ ከብሩንዲ ቡድን ጋር በተደረገው ጨዋታ የአዘጋጇ ሀገር ዳኞች መዳኘታቸው ቅሬታ ፈጥሮብናል። ያም ሆኖ ግን ቡድኔ ጨዋታውን አሸንፏል።” የሚሉት አሠልጣኝ ፍሬው ከውድድሩ በርካታ ትምህርቶች እንደቀሰሙም ተናግረዋል። “ውድድሩ እንደመጀመሪያ ተሳታፊነታችን ብዙ ነገር ቀሰምንበታል። ውድድሩ ላይ ብሔራዊ ቡድኖች ምን አይነት አቋም ላይ እንዳሉ አይተናል። ለአብነትም ታንዛኒያን የመሰሉ ተጋጣሚዎች ቡድናችን ምን አቋም ላይ እንዳለ ያሳየን ነው። በሌሎቹ ብሔራዊ ቡድኖች ያየናቸው ጠንካራ ጎኖችም ትምህርት ሆነውናል። ይህን ውድድር በቀጣይ ለሚጠብቀን ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎችም በደንብ ተጠቀምንበታል፤ ጥሩ ግብዓት የሚሆኑንም ነገሮች ያየንበት በመሆኑ ለሱም የተሻለ ቡድን ይዘን እንድንቀርብ ረድቶናል።” ብለዋል።
አሠልጣኝ ፍሬው ሀሳባቸውን ቀጥለው ጨዋታዎች በየአንድ ቀን ልዩነት መደረጉ ጉዟቸውን እንዳከበደው ገልፀው ”በዚህ ላይ ከተጫወትናቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱ በቀትር ላይ መሆኑ ጫና ነበረው። ውድድሩ ላይ የሁለት ቀን እረፍት ቢኖረው ሪከቨር ለማድረግ የተሻለ እድል ይፈጥራል። ያም ሆኖ የተሰራው ስራ ውጤታማ አድርጎናል። ምክንያቱ ደሞ ብሔራዊ ቡድን ‘ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ እንደሚባለው አይደለም የተሰራው። ፌዴሬሽኑ በሀዋሳ በነበረው ውድድር ቀድመን ተጨዋቾች እንድንመለምል ዕድል አመቻችቶልን ነበር። በዚህ አጋጣሚ የፌዴሪሽኑ አመራሮች አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ እንዲሁም ዶ/ር ሳሙኤል የሸዋስ ቡድኑን ስሰራ በቅርብ ርቀት ነበሩ። ከዚህ በላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ላይ ለውጥ ለመፍጠር እየጣሩ ያሉት ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳይያስ ጂራንም በጣም ማመስገን እፈልጋለው። ስፖርተኛ መያዝ እና ማውራት የሚችሉ ሰው ናቸው። በአካል መጥተው ቡድኑን ስለጎበኙ እና ስላበረታቱም እናመስግናለን። በዚሁ አጋጣሚ ስራ አስፈፃሚውም አምኖብኝ እድል ሰጥቶኝ ለኢትዮጵያ እንድሰራ ስላደረገኝ አመስግናለሁ።” ሲሉ ለውጤታማ ጉዟቸው ከጎን በመሆን ያገዟቸውን አመስግነዋል።
በውድድሩ ላይ ለብሔራዊ ቡድን አዲስ የሆኑ ተጫዋቾችን በአዛኙ መጠቀማቸውን የሚገልፁት አሰልጣኝ ፍሬው ይህ ያደረጉት በብሔራዊ ቡድን መተካካት እንደሚቻል ለማሳየት መሆኑን ጠቁመዋል። “በውድድሩ ላይ የተጠቀምናቸው ተጫዋቾች አምስቱን ብቻ ነባር ተጫዋቾችን ነው የተጠቀምነው። ከዛ ውጭ 15 ተጨዋቾች በብሔራዊ ቡድኑ አዲስ ናቸው። ይህን ማድረጋችን ብሔራዊ ቡድን መተካካት እንደሚቻል ለማሳየት ነው። ከተጋገዙ እና አብረው ከሰሩ ሩቅ መጓዝ ይቻላል። ”
ዛሬ የሚደረገው የመጨረሻ ጨዋታን ማሸነፍ ብቻ ኢትዮጵያን የውድድሩ ቻምፒዮን ያደርጋታል። አሰልጣኙም ይህን በመረዳት ለማሸነፍ ብቻ የሚጫወት ቡድን ይው እንደሚገቡ ይናገራሉ። ” ከጨዋታው ከኛ ማሸነፍን ጠብቁ። በጨዋታው የእኛ አማራጭ ማሸነፍ ብቻ ነው፤ አቻ እንኳን ለእነሱ ነው አድቫንቴጁ። ከዚህ አንፃር ይዘነው የምንገባው ቡድን ቶሎ ቶሎ የሚያጠቃ እና የተገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም የሚችል ቡድን ይሆናል። እነሱ በሀገራቸው እና በሜዳቸው ነው የሚጫወቱት። ሆኖም ሀገራችን ይህ ዋንጫ ይበልጥ ያስፈልጋታል። ይህ ዋንጫ ኢትዮጵያዊያን አንድ መሆናችን እና ጥንካሬያችንን የምናሳይበት ነው ። እኛ በስነ ልቦናውም ሆነ በቴክኒክካዊ ጉዳዮች ላይ ተዘጋጅተናል። ብዙም ችግር አይገጥመንም ብዬ አስባለሁ። ሆኖም በእግርኳስ የሚመጣውን ሁሉ በፀጋ ለመቀበልም ተዘጋጅተናል።” በማለት ቆይታቸውን አሳርገዋል።