አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ይመራሉ

ኢትዮጵያዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ለመምራት ወደ ራባት ያመራሉ፡፡

በኳታር አስተናጋጅነት ለሚደረገው የ2022 የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ አህጉር የማጣሪያ ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡ በማጣሪያው ምድብ አምስት ላይ በአስር ነጥብ እና በስምንት ነጥብ ተከታትለው የሚገኙት ማሊ እና ዩጋንዳ የፊታችን ዕሁድ ኅዳር 5 ምሽት 1፡00 ላይ የሚያደርጉትን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታም አራት ኢትዮጵያዊያን በዳኝነት ይመሩታል፡፡

ማሊ ሜዳዋ በካፍ በተጣለባት ዕገዳ ምክንያት ሞሮኮ ራባት ላይ በሚገኘው ስታድ አድራር የተሰኘው ግዙፉ ስታዲየም ላይ የሚደረገውን ይህን የሁለቱን ሀገራት ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ባምላክ ተሰማ በረዳት ዳኝነት ደግሞ ትግል ግዛው እና ተመስገን ሳሙኤል፣ በአራተኛ ዳኝነት በላይ ታደሰ እንዲመሩት በካፍ መመረጣቸውን አረጋግጠናል፡፡

አራቱም ዳኞች የፊታችን ሐሙስ ወደ ስፍራው የሚያመሩ ሲሆን አይቮሪስታዊ ኮሚሽነር ደግሞ ለጨዋታው ታዛቢነት መመደባቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡