ለ82 ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር የተጫወተችው ኢትዮጵያ የሴካፋ ቻምፒዮን ሆናለች

በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ለረጅም ደቂቃዎች የተጫወተችው እና የመጀመሪያውን አጋማሽ ሁለት ለባዶ ስትመራ የነበረው ኢትዮጵያ ዩጋንዳን በመርታት የሴካፋ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር አሸናፊ ሆናለች።

ጨዋታው ገና በተጀመረ በስምንተኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከባድ ፈተና ውስጥ የገባበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም የዩጋንዳዋ ፈጣን አጥቂ ፋውዚያ ናጄምባ ተከላካዮችን አምልጣ ወደ ግብ በመሄድ ከግብ ዘቧ እየሩሳሌም ሎራቶ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ አልፋ ግብ አስቆጥራለው ስትል እየሩሳሌም ጥፋት ትሰራባታለች። የዕለቱ ዳኛም በቅድሚያ ጥፋቱን አምና ለግብ ዘቧ የቢጫ ካርድ ማስጠንቀቂያ ብትሰጣትም ረዳት ዳኛዋ ሀሳቧን አስቀይራት እየሩሳሌም በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ እንድትወጣ ሆኗል።

የኢትዮጵያን የግብ ዘን የቀይ ካርድ ሰለባ ያደረገውን ቅጣት ምትም ኮሙንታሌ ሱማያህ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መትታው ተቀይራ የገባችው ምህረት ተሰማ አድናዋለች። በ20ኛው ደቂቃም ዩጋንዳዎች ከግራ መስመር መነሻን ባደረገ ጥቃት በአምበላቸው ፋውዚያ ናጄምባ አማካኝነት ሌላ የሰላ ሙከራ አድርገዋል።

ሳይጠበቅ ገና በጊዜ የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በመዓድን ሳህሉ አማካኝነት ከሞከሩት ሙከራ በተጨማሪ ሌላ ጥቃት ለመሰንዘረ 35 ደቂቃዎችን መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። ከዛ በፊት ግን ዩጋንዳ ወደ መሪነት የተሸጋገረችበትን ጎል አግኝታለች። በዚህም በ26ኛው ደቂቃ ናንዴዴ ዛይና በቀኝ መስመር እየገፋች የሄደችውን ኳስ ሳጥኑ ውስጥ ራሷን ነፃ አድርጋ ስትጠብቅ ለነበረችው ናንዳጎ ሀዲጃ ሰጥታት ሀዲጃ በግራ እግሯ ኳስ እና መረብን አገናኝታለች። ከላይ እንደጠቀስነው የአሠልጣኝ ፍሬው ተጫዋቾች በ35ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከቅጣት ምት ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል።

አጋማሹ ሊገባደድ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ዩጋንዳ መሪነቷን ወደ ሁለት ከፍ ያደረገችበትን ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይራለች። በዚህም አምበሏ ፋውዚያ ናጄምባ ከወደ ግራ ያዘነበለውን የቅጣት ምት በቀጥታ ስትመታው ግብ ጠባቂዋ ምህረት መልሳው የነበረ ቢሆንም ኳሱ በሚገርም ሁኔታ ወደ ፊት ነጥሮ አቅጣጫ በመቀየር ወደ ኋላ በመጓዝ መረብ ላይ አርፏል። አጋማሹም በዩጋንዳ ሁለት ለምንም መሪነት ተገባዷል።

የሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ተነሳሽነት የቀረቡት ኢትዮጵያዎች እጅግ የጎዳቸውን የቁጥር ብልጫ ተቋቁመው ኳስን ማንሸራሸር ይዘዋል። ከዚህ በተጨማሪም በርከት ብሎ ወደ ዩጋንዳ ሜዳ በመግባት ክፍተቶችን መፈለግ ጀምረዋል። በ51ኛው ደቂቃ ዩጋንዳ የሰነዘረችውን እጅግ አደገኛ ኳስ በማምከን በፍጥነት ወደ እንቅስቃሴ የገቡት ተጫዋቾቹም ኳስ እና መረብን አገናኝተው በጨዋታው ያላቸውን ህይወት አራዝመዋል። በዚህም አጥቂዋ ረድኤት አስረሳኸኝ ፍጥነቷን ተጠቅማ ተከላካዮችን አፈትልካ በመውጣት ያገኘችውን ኳስ በጥሩ እርጋታ ከሳጥን ውጪ በግብ ዘቧ ንያዬንጋ ዳፊን አናት በመላክ ግብ አድርጋዋለች።

በዚሁ የእንቅስቃሴ ብልጫ መጫወት የቀጠሉት ተጫዋቾቹም በቶሎ አቻ ለመሆን መታተራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ግቡን ካስቆጠሩ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ረድኤት ቱሪስት ለማ የተቀበለችው እጅግ ጥሩ ኳስ ለጥቂት ሳትጠቀምበት የቀረች ሲሆን ከደቂቃ በኋላ ደግሞ መሳይ ተመስገን ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶታል። በተቃራኒው ተዳክመው የታዩት ዩጋንዳዎች ደግሞ በ67ኛው ደቂቃ በፋውዚያ ናጄምባ አማካኝነት ዳግም መሪነታቸውን ለማስፋት ጥረው መክኖባቸዋል።

ከደቂቃ ደቂቃ እድገት እያሳዩ የተጫወቱት ኢትዮጵያዎች በ68ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ ታደሠን ቀይራ ወደ ሜዳ የገባቸው አርያት ኦዶንግ በ79ኛው ደቂቃ ቡድኗን አቻ አድርጋለች። ተቀይራ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ጨዋታውን መቀየር የጀመረችው አርያት ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በግራ መስመር ወደ ዩጋንዳ የግብ ክልል እየገፋች ሄዳ ለመሳይ ያቀበለቻትን ኳስ መሳይ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችው ቱሪስት ለማ አቀብላት ኢትዮጵያ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች። በቀሪ የጨዋታው ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በአሠልጣኝ ፍሬው የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዩጋንዳን አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።

ድሉን ተከትሎ በሴቶች ዘርፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የሴካፋ ዋንጫን በማንሳት ታሪክ ፅፏል። በስድስት ቡድኖች መካከል በተደረገው ውድድር ላይ 11 ግቦችን ያስቆጠረችው የዩጋንዳዋ ፋውዚያ ናጄምባ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ስታጠናቅቅ የኢትዮጵያ ተከላካይ ብርቄ አማረ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጣለች።

ያጋሩ