ለ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የአቀባበል እና ዕውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል

“ጠንካራ መሆናችሁን ስላስመሰከራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” አቶ ቀጀላ መርዳሳ

“የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ከፍተኛ ነው፤ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት በላይ ነው።” አቶ ኢሳይያስ ጅራ

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድርን አሸንፎ ለመጣው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምሽት ላይ በጁፒተር ሆቴል የአቀባበል እና ሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ የገቡት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በመዲናዋ ጎዳናዎች ተዟዟረው በመጨረሻም በጁፒተር ሆቴል በተዘጋጀው የዕውቅና አሰጣጥ እና የዕራት ግብዣ ፕሮግራም አልፈዋል። በምሽሩ ዝግጅትም የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፣ ሚኒስቴር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ” ከባድ ስሜት ነው ያለው፤ ከአዘጋጅ ጋር ለፍፃሜ ደርሰህ ዋንጫ ይዘህ ስትመጣ ከማሸነፍም በላይ ትርጉም አለው። በተለይ አሁን ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያንን ካሉበት ድብርት ውስጥ የሚያስወጣ አይነት ውጤት ነው ብዬ ነው የማምነው። በዚህው አጋጣሚ ልጆቹን ማመስገን እፈልጋለሁ። ብታይዋቸው በጣም ልጆች ናቸው፤ ነገር ግን የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ከፍተኛ ነው፤ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት በላይ ነው ስሜታቸው። አግብተው የሚያለቅሱ እና ለተጨማሪ ድል እና ትግል የተጠሙ ናቸው። እኔ በግሌ እንደ እግርኳስ አመራር ደስተኛ ነኝ። ለኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ማለትም እፈልጋለሁ ” ብለዋል።

በማስከተል የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው “በወኔ በፅናት ባትንደረደሩ ኖሮ የማሸነፉ እድል ጠባብ ነበር። በእግርኳስም ሆነ በሌላው ዘርፍ ለማሸነፍ ወኔ ያስፈልጋል። ለማሸነፍ ሁለት ነገር ያስፈልጋል፤ የአካል ጥንካሬ እና በመንፈሰ ጠንካራ መሆንን ይጠይቃል። እናሸንፋለን ብለን ካመንን እናሸንፋለን። ከፊታችንም የምናሸንፈው አለ እናሸንፋለን። ሴቶች ከወንዶች እኩል ጀግኖች ጠንካሮች እንደሆኑ እና ሁሉንም ነገር ከወንዶች እኩል ማድረግ እንደሚችሉ ይህ ውጤት ማረጋገጫ ነው። ጠንካራ መሆናችሁን ስላስመሰከራቹ እንኳን ደስ አላችሁሁ ማለት እፈልጋለው።” ብለዋል።

በመቀጠል በዕለቱ የክብር እንግዳ አማካኝነት ለቡድኑ አባላት የማበረታቻ ሽለማት የተበረተ ሲሆን ለዋና አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል አንድ መቶ ሺህ ብር፣ ለረዳት አሰልጣኞች ሰባ ሺህ ብር፣ ለቴክኒክ ባለሙያ ሰባ አምስት ሺህ ብር፣ ለቡድን መሪው አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ሰባ ሺህ ብር፣ ለተጫዋቾች ለእያንዳንዳቸው ስልሳ ሺህ ብር፣ ለህክምና ባለሙያዎች ሀምሳ ሺህ ብር ተበርክቷል። ከተጠቀሱት ውጪ ላሉ አባላት የተበረከቱ ሽልማቶችን ጨምሮም በድምሩ 1.8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የሽልማት መርሐ ግብር በኬክ ቆረሳ ተገባዷል።