የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ኮከብ ተጫዋች በመሆን የተመረጠችው ብርቄ አማረ ኮከብ መባሏ የፈጠረባትን ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርታለች።
ሻሸመኔ ከተማ ተወልዳ ያደገችው እና የእግርኳስ ህይወቷን በክለብ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ ጀምራ በሻሸመኔ ከተማ በኃላም በአቃቂ ቃሊቲ አንድ ዓመት ቆይታ በማድረግ አሁን በድሬዳዋ ከተማ እየተጫወተች ትገኛለች። በሴካፋው ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በመከላከሉ ረገድ ስኬታማ ቆይታ በማድረጓ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆና የተመረጠችው ብርቄ አማረ ተከታዩን አስተያየት ሰጥታናለች።
አጠቃላይ ውድድሩ ምን ይመስል ነበር?
እጅግ በጣም ደስ ይል ነበር። ፈጣሪ መርጦን ለዚህ ቀን ደርሰናል ብዬ አምናለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን ብዙ ጫናዎች ቢኖሩም እነሱን ተቋቁመን ለዚህ ቀን ደርሰናል።
የውድድሩ ኮኮብ እሆናለሁ ብለሽ ጠብቀሽ ነበር ?
በእርግጥ ኮከብ እሆናለው ብዬ አላሰብኩም ነበር። ከኔ የተሻሉ በርካታ ተጫዋቾች፤ ብዙ ግቦችን የሚያስቆጥሩ ነበሩ። እኔ ከኋላ መስመር ነው ኮኮብ ሆኜ የተመረጥኩት። እርግጥ ነው ግብ እንዳይቆጠርብን ተፅዕኖ ፈጥሬያለሁ። ቢያንስ ከአምስቱ ጨዋታ ውስጥ ሦስት ጎሎች ብቻ ነው የተቆጠሩብን። ብቻ እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ነገር ሰርተናል። ለሀገራችን ከዚህም በላይ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ።
በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያዋ ኮኮብ ተጫዋቾች ነሽ። ምን አይነት ስሜት ፈጥሮብሻል ?
ለኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው፤ ቃላት ያጥረኛል። እንደዚህ ብዬ ለማውራት አልችልም። ብቻ ለኔ ታሪክ ነው። ሀገራችን እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት እንደዚህ አይነት ውጤት ማምጣታችን በጣም እድለኝነት ነው። እውነት በኢትዮጵያዊነቴ በጣም ነው የኮራሁት።
ስለቀጣይ ምን ታስቢያለሽ ?
የእግርኳስ ህይወቴ በዚህ ስኬት ብቻ አይቆምም። ጠንክሬ በመሥራት ሀገሬን ለማስጠራት፤ ሌሎች ዋንጫዎችንም ለማሳካት አስባለው።