ጋናን የሚፋለመው የኢትዮጵያ የመጀመሪያ አሰላለፍ ታውቋል

ደቡብ አፍሪካ ላይ ከጋና አቻው ጋር የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍን ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታለች።

ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 7 ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እያሉት ከወዲሁ መውደቁ ይታወቃል። ይህ ቢሆንም ቡድኑ ዛሬ እና የፊታችን እሁድ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎቹን ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ያደርጋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በብቸኝነት የምትጠቀምበት የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መታገዱን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ኦርላንዶ ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ ላይም የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ የመረጧቸው የመጀመሪያ አስራ አንድ ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው።

በግብ ብረቶቹ መሐል ተክለማርያም ሻንቆ እንዲቆም ሲደረግ ከፊቱ ደግሞ ረመዳን የሱፍ፣ አስቻለው ታመነ፣ ምኞት ደበበ እና አሥራት ቱንጆ እንዲሰለፉ ሆኗል። በሦስትዮሽ ጥምረት በተዋቀረው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ላይ ደግሞ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ሽመልስ በቀለ እና መስዑድ መሐመድ ተሰልፈዋል። የቡድኑን የፊት መስመር አምበሉ ጌታነህ ከበደ ሲመራው በሁለቱ መስመሮች ደግሞ አቡበከር ናስር እና ዳዋ ሆቴሳ እንዲሰለፉ ተደርጓል።