ገላን ከተማ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሟል

ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ በከፍተኛ ሊግ የመጀመርያ ሥራውን ከገላን ከተማ ጋር ለመሥራት ስምምነት አድርጓል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ከሆኑት ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር የጥትቅ አቅርቦት ስምምነት የፈፀው ጎፈሬ ስፖርት በዛሬው ዕለት በከፍተኛ ሊጉ ገላን ከተማ ጋር አብሮ ለመሥራት ይፋዊ ስምምነት ተፈራርሟል።

ቦሌ ሮቤል ፕላዛ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ቢሮ በተደረገው የስምምነቱ ይፋዊ ፕሮግራም ላይ በገላን ከተማ በኩል ፕሬዝዳንቱ አቶ ደሣለኝ ጥላሁን፣ በጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች በኩል አቶ ሳሙኤል መኮንን በመገኘት ሁለቱ አካላት አብረው መሥራት መጀመራቸውን የሚያረጋግጥ ውል ተፈራርመዋል።

“ማሸነፍ ልማድ ነው” በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው ጎፌሬ ለሁለት ዓመት በሚቆየው ስምምነት ለዋናው እና ለተስፋው ቡድን እንዲሁም ለአትሌቲክስ ቡድኑ የመጫወቻ መለያዎች፣ የልምምድ፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች፣ የመመገቢያ እንዲሁም የጉዞ ማልያዎችን የሚያቀርብ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ አካላት የደጋፊ ማልያ ሽያጭን በተመለከቱ የማርኬቲንግ ስትራቴጂዎች ላይም አብረው እንደሚሰሩ ተገልፅዋል።

የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ደሣለኝ ጥላሁን ገላን ከከፍተኛ ሊግ የመጀመርያው ክለብ በመሆን ከጎፈሬ ጋር በመስማማቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ”የገላን ከተማን ስፖርት ማሳደግ ዋና አላማችን ነው። ይህ ስምምነት በርከት ያሉ ዘርፎች የተካተቱበት ነው። በአጠቃላይ የክለባችንን ስም ከፍ ለማድረግ እና ህዝባዊ መሠረት ያለው እንዲሆን እንዲህ ያሉ ስምምነቶች አስፈላጊ ናቸው። ወደፊትም ከጎፈሬ ጋር አብረን እየሠራን የከተማችንን ስፖርት እናሳድጋለን። በተጨማሪ በከተማችን ያሉትን ባላሀብቶች ወደ ስፖርቱ እንዲገቡ ለማስቻል ሰፊ እቅድ አውጥተን እየሰራን ነው።” ብለዋል።

የጎፈሬ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው “በፕሪምየር ሊጉ ከስድስት ቡድኖች ጋር አብሮ በመሥራት ያለንን አጋርነት አሁን ደግሞ ወደታችኛው ሊግ ወርደን ለመጀመርያ ጊዜ ከገላን ከተማ ጋር ለሁለት ዓመት የሚቆይ ስምምነት በመፈፀም አስቀጥለናል። ከዚህ ስምምነት በተጨማሪም በሌሎች ዘርፎች አብረን እንደምንሰራ ተነጋግረናል። ይህ ስምምነት በገላን ከተማ ብቻ የሚቆም አይደለም። በሰፊው ሁሉንም የከፍተኛ ሊግ ቡድኖችን የመያዝ ዕቅድ አለን። ከአብዛኛዎቹ ጋር ተነጋግረን የዲዛይን ሥራዎችን ጨርሰናል። የሚቀረን ይፋዊ ስምምነት ማድረግ ብቻ ነው። ጎፈሬ በተሻለ ጥራት ትጥቆችን እያቀረበ ይቀጥላል። ብለዋል።