በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የተላለፈበትን ውሳኔ በመቃወም የይግባኝ አቤቱታ ያሰማው ሀድያ ሆሳዕና ውሳኔው ፀንቶበታል።
በ2013 የውድድር ዘመን ሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከሚያዚያ ወር አንስቶ ከኃላፊነታቸው በማንሳት የተለያዩ ከደሞዝ ጋር የተያያዙ ጥቅማጥቅሞችን አግዶ መቆየቱ ይታወሳል። በአንፃሩ አሰልጣኝ አሸናፊ ”የተወሰነብኝ ውሳኔ ተገቢ አይደለም” በማለት ያቀረቡት ቅሬታ በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት አግኝቶ ክለቡ በአሰልጣኝ አሸናፊ ላይ የወሰነው ውሳኔ ውድቅ መደረጉ ይታወቃል።
የዲሲፒሊን ኮሚቴው በወሰነው ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት ሀዲያዎች አቤቱታቸውን ወደ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አቅርበዋል። በሌላ በኩል አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአቶ ብርሐኑ በጋሻው የሕግ አማካሪ ጠበቃ እና የአግርኳስ ተጫዋቾች ሕጋዊ ወኪል አማካኝነት ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በመጨረሻም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የዲሲፕሊን ኮሚቴው በሁለቱ አካላት መካከል አስቀድሞ የወሰነው ውሳኔ የፀና መሆኑን በማረጋገጥ አሰልጣኝ አሸናፊ ከተሰናበቱበት ጊዜ አንስቶ የውል ዘመናቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ ያለው ጥቅማቸው እንዲጠበቅ ለሀዲያ ሆሳዕና የውሳኔ ደብዳቤ ልኳል።