ኢትዮ ኤሌክትሪክ አስር አዳዲስ ተጫዋቾች ሲያስፈርም የነባሮችን ኮንትራትም አድሷል፡፡
በተጠናቀቀው የ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ በምድብ ሀ ስር ከነበሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀድሞ ወደገነነበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም ለመመለስ ብርቱ ፉክክር ማድረግ ቢችልም በመከላከያ ተበልጦ ሳይሳካለት ቀርቷል። ቡድኑ ለ2014 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየተመራ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን ተጠናክሮ ለመቅረብ በማለም አስር አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ ሲቀላቅል የሰባት ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት በማራዘም አምስት ታዳጊዎችን ከተስፋ ቡድኑ አሳድጓል፡፡
ክለቡ ካስፈረማቸው አዲስ ተጫዋቾች መሀል አንጋፋው አማካይ ምንያህል ተሾመ ይጠቀሳል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ድሬዳዋ እና ወልድያ የመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ከጊዜያት የሜዳ ላይ መራቅ በኋላ በኤሌክትሪክ ያገኘውን የሙከራ ጊዜ አገባዶ ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡
የቀድሞው የደደቢት፣ ወላይታ ድቻ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት እስከ አጋማሹ ድረስ በአዳማ ከተማ ቆይታ የነበረው ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት እንዲሁም የቀድሞው የባንክ፣ መቐለ፣ ድሬዳዋ እና ወልዋሎ አዲግራት የመሀል ተከላካይ በመሆን ከዚህ ቀደም ያገለገለው ፍቃዱ ደነቀ ሌሎች ክለቡን የተቀላቀሉ አዲስ ፈራሚዎች ናቸው።
በአርሲ ነገሌ፣ መከላከያ፣ በጅማ አባ ቡና፣ መቐለ 70 እንደርታ እና በወልዋሎ አዲግራት እንዲሁም ባለፈው ዓመት በድጋሚ ለቀድሞው ክለቡ መከላከያ በመጫወት ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው ካርሎስ ዳምጠው፣ የሰበታ ከተማዎቹ ናትናኤል ጋንቹላ እና ኢብራሂም ከድር ክለቡን ተቀሌቅለዋል።
ተስፋፅዮን ፋንታሁን (ተከላካይ ከስልጤ ወራቤ)፣ ተስፋዬ ሽብሩ (ተከላካይ ከኢኮሥኮ)፣ ፊልሞን ገብረፃድቅ (አጥቂ ከአቃቂ ቃሊቲ) እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ተመስገን ካስትሮ ታናሽ ወንድም የሆነው ተከላካዩ ከፍያለው ካስትሮ ሌሎች የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ፈራሚዎች ናቸው፡፡
ፀጋ ደርቤ፣ ስንታየው ዋለጬ ፣ ሳሙኤል ታዬ ፣ አቤል ታሪኩ ፣ ቢኒያም ትዕዛዙ ፣ ቢኒያም ታከለ እና ዘሪሁን ታደለ ውላቸው ሲራዘምላቸው ተመስገን ያዕቆብ ፣ ያሬድ የማነ ፣ አንዋር ሙራድ ፣ ኪሩቤል ኃይሌ እና ኃይለሚካኤል በሱፈቃድ የተባሉ ታዳጊዎችን ከታችኛው የክለቡ ቡድኖች ማደግ መቻላቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው ዝርዝር መረጃ ገልጿል፡፡