አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በድል ያጠናቀቁትን ውድድርን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል

👉 “ራቅ ብዬ ብቀመጥም ማንነታቸውን በደንብ የማላቃቸው ሰዎች መጥተው መልበሻ ክፍል አስገብተው እንዲቆለፉብኝ አደረጉ”

👉”ተጫዋቾቹ ሀገር ወዳዶች ስለነበሩ ጫናውን ተቋቁመው ይህንን ድል አስመዝግበዋል”

👉”…ከዛ በኋላ ወደ ውስጥ ስገባ ለቅሶ ቤት ነበር የሚመስለው”

👉”…የሚገርመው ፊሽካ ተነፍቶ ወደ ሜዳ ስገባ የማላውቃቸው አራቱ ሰዎች ድጋሜ እየሮጡ መተው ያዙኝ። ምንድን ነው ሲባሉ የሚታሰር መስሎን ነው አሉ”

የሴካፋን ዋንጫ ለሀገራችን ያመጡት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በዛሬው ዕለት ውድድሩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በስድስት የቀጠናው ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ሲደረግ የነበረው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ውድድር ሀገራችን ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርጎ ከሦሰት ቀናት በፊት መጠናቀቁ ይታወቃል። በውድድሩ ጠንካራ ብቃት ያሳየው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ከትናንት በስትያ ወደ ሀገራችን የገባ ሲሆን በፌዴሬሽኑ የምስጋና እና የእውቅና ዝግጅት ተሰናድቶለት እንደነበረም ይታወሳል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ደግሞ ዛሬ ከሰዓት ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ውድድሩን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። በአሠልጣኙ በቅድሚያም ዝግጅታቸውን በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል።

“ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሩዋንዳ ጋር ከተጫወትነው ጨዋታ በኋላ የ12 ቀን ጊዜ ነበረን። ሴካፋ ላይ እንደምንወዳደር ከተነገረን በኋላም ያሉትን ተጫዋቾች ማስቀጠል እና ሦስት አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማምጣት ሞክረናል። የተጨመሩትም ተጫዋቾች ለቡድኑ አዲስ የነበሩ ናቸው። በነበረን 12 ቀን ጁፒተር ሆቴል እና የካፍ የልዕቀት ማዕከል በመቀመጥ ዝግጅታችንን አድርገናል። ዩጋንዳ ከገባን በኋላም ውድድሩ አሰልቺ እና አድካሚ በመሆኑ ብዙ የልምምድ መርሐ-ግብር አልነበረንም።”

አሠልጣኝ ፍረው ቀጥለው ቡድናቸው ዋንጫ ማምጣቱን ተከትሎ “ይህንን ውጤት ያገኘነው ባለመድነው ነገር ተጫውተን ነው። ካደረግናቸው 5 ጨዋታዎች ሁሉንም በድል ተወጥተን መጥተናል። ለዚህ ደግሞ ፈጣሪን ማመስገን እፈልጋለሁ። እግርኳስ ቅንነት ይጠይቃል። ወደ ዩጋንዳ የተጓዝነው ሁሉ ለሀገራችን ይህ ዋንጫ እንደሚያስፈልጋት ስለምናውቅ በቅንነት ተጋግዘን ዋንጫውን ይዘን መጥተናል።” ብለዋል።

አጭር ደቂቃ ከፈጀው የአሠልጣኙ ገለፃ በኋላ ተከታዮቹ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስተው ምላሽ መሰጠት ተጀምሯል።

ስለተመዘገበው ድል…?

“ሁለት አይነት ስሜት ነበረው። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን። ኢትዮጵያዊያን በመሆናችን ብቻ ደግሞ ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል። የደስታ ጉዳይ እንደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ይህ ግን የሀገር ጉዳይ ስለሆነ ልኬቱ ትልቅ ነው። እኔም በተለይ ሁለተኛው ጎል ሲገባ ትንሽ ስሜቴን መቆጣጠር ተስኖኝ ነበር። እርግጥ የነበረው ነገር ትንሽ ደስ አይልም ነበር። የሆነው ሆኖ በድሉ እጅግ ደስተኞች ነን።”

ውድድሩ ላይ ስለነበረው ጫና…?

“ምንም ጥያቄ የለውም ሁላችንም የምንናገረው ነው። ጫና ነበረው። በማናውቀው ባህል እና የአየር ዘባይ ነበር የተጫወትነው። ከምንም በላይ ደግሞ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታችንን በእግርኳስ ከባድ ሰዓት በሆነው 7:30 ላይ ነበር የተጫወትነው። ከዛ በሦስተኛው ጨዋታ ታንዛኒያን ስንገጥም ተጫዋቾቹ በሁለቱ የቀን ጨዋታዎች ጨርሰው ነበር። ድካሞች ነበሩ። ውድድሩ ደግሞ አንድ ቀን ተጫውተህ አንድ ቀን የምታርፍበት ነበር። ይህ ከባድ ነው። ባለን አቅም ግን ተጫዋቾቹ እንዴት ቶሎ ሪከቨር ማድረግ አለባቸው የሚለውን ስንሰራበት ነበር። ከዚህ ውጪ ቅድም ያልኩት የባህል ጉዳይም ስለነበር የምግብ ችግርም ነበር። ተጫዋቾቹን ቀስ እያልን አለማምደን ነው ወደ ጥሩ ነገር የገባነው። ብቻ ሙቀቱ የጨዋታ እና የልምምድ ሰዓቶቹ ትንሽ ከበድ ይሉ ነበር። ተጫዋቾቹ ግን ሀገር ወዳዶች ስለነበሩ ጫናውን ተቋቁመው ይህንን ድል አስመዝግበዋል።”

ስለ ተጋጣሚ ቡድኖች ብቃት…?

“የተጋጣሚ ትልቅ እና ትንሽ የለውም። ውድድሩም ይህንን አሳይቷል። የውድድሩም ቅርፅ ተጫዋቾችን እያፈራረክ እንድትጠቀም ዕድል አይሰጥክም። ምክንያቱም ጠንካራ ቡድንህን መጠቀም ስለሚጠይቅ። በአጠቃላይ ከጂቡቲ ውጪ ያሉት ቡድኖች ጠንካሮች እና ተቀራራቢ ነገር ያላቸው ናቸው። ጂቡቲዎችም ወጣቶች ስለሆኑ ነገ ማስተካከል ይችላሉ። እግርኳስ በሰራከው ልክ ነው የሚከፍልህ። ታንዛኒያዎች ግን እጅግ ጠንካሮች ነበሩ። በሁሉም ክፍሎች የተደራጁ ነበሩ።”

በፍፃሜው ጨዋታ ስለተከሰቱት ነገሮች?

“እኔ አሠልጣኝ ነኝ። የዳኝነት ስራ ውስጥ አልገባም። ግን እንዲሁ ከምናየው እና ከምናነበው ነገር ቀይ ካርዱ አልተዋጠልኝም። ግን ህግን መቀበል ስላለብን ተቀበልን። ከዛ በኋላ ጎዶሎ ነበርን። እኛ ጎዶሎ ከሆንን በኋላ ዩጋንዳዎች ጎል ያገቡብንም በእውቀት አይደለም። ካለመግባባት ችግር የገባብን ነበር። ከዚህ ውጪም የትኩረት ማነስ ችግር ነበር። በአጠቃላይ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረን ነገር ጥሩ አልነበረም። ተጫዋቾቹ ትንሽ ስሜታዊ ሆነው ነበር። ሁለት ሦስት ተጫዋቾች እንደውም ሊያለቅሱ ሁሉ ነበር። እኔ እንደውም ከኳሱ ይልቅ እነሱን ማገዱ ላይ ነበርኩ። እንደምንም ሆኖ ብቻ አጋማሹ አለቀ እና ወደ መልበሻ ክፍል አመራን። ለዶክተሮች ምናምን የምትሰጠው ደቂቃ አለ። ከዛ በኋላ ወደ ውስጥ ስገባ ግን ለቅሶ ቤት ነበር የሚመስለው። አስሩም ተጫዋቾች በጣም አዝነው ነበር። ሊያዳምጡኝ እንኳን አልቻሉም ነበር። በጣም ነው የምንከባበረው ግን በዛ ሰዓት ብናገር ብናገር የሚያዳምጠኝ ሰው አጣሁ። ከዛ በኋላ የመጨረሻ እነሱን ለመሳቢያ ‘አሁን ካልሰማችሁኝ የሀገር ገፅታ ይበላሻል’ አልኳቸው። የሀገር ገፅታ እንዳይበላሽም በትክክል እንዲጫወቱ ነግሬ የኳስ ቁጥጥራቸው በትክክለኛው ቦታ እንዳልሆነ ነግሬያቸው እንዲያስተካክሉት አስታውሼ የማጥቃቱ ላይ ያለን ነገር እንዲስተካከል ተማምነን ወጣን። በዚህ አጋጣሚ አቶ ኢሳይያስ ጂራንም ማመስገን እፈልጋለሁ። ተጫዋቾቹ ምንም እንዳይሰማቸው እና በቻሉት አቅም እንዲጫወቱ አበረታቷቸው ነበር።

“ከእረፍት በኋላ ደግሞ ያያችሁት ተፈጠረ። ተከላካዮቹ ስህተት እንደሚሰሩ ነግሬያቸው ነበር። በነገርኳቸው መንገድ ጎሉ ተቆጠረ። ዩጋንዳዎች ሦስት ጥቅም ነበራቸው። ማሸነፍ፣ አቻ መውጣት እና የቁጥር ብልጫ። ይህንን ታሳቢ በማድረግ እየተመራን እናሸንፋለን የሚል ነገር እውነት ለመናገር አልነበረኝም። አቻ መውጣትም ለእኔ ሀገርን ማኩራት ነበር። ይህንን ተከትሎም አቻ ለመሆን ተከላካይ ቀንሰን አጥቂ አስገባን። ፈጣሪ ፈቅዶ ለውጣችን ሰርቶ አቻ ሆነ። የተጫዋች ብቻ ሳይሆን ቀዩ እኔም ጋር መጣ። ትንሽ ህግ የተጣሰበት ነገር ነበር። ራቅ ብዬ ብቀመጥም ማንነታቸውን በደንብ የማላቃቸው ሰዎች መጥተው መልበሻ ክፍል አስገብተው እንዲቆልፉብኝ ትዕዛዝ አስተላለፉ። ሦስተኛው ጎል የገባው እንደውም ከእነሱ ጋር እየተከራከር ነው። ብቻ በሚገርም ሁኔታ መልበሻ ክፍል ነው ተቆልፎብህ የምትቀመጠው አሉኝ። ምን አይነት ህግ እንደሆነ ባላውቅም ይህ ሆነ። የሚገርመው ፊሽካ ተነፍቶ ወደ ሜዳ ስገባ እንኳን አራቱ ሰዎች ድጋሜ እየሮጡ መተው ያዙኝ። ምንድን ነው ሲባሉ የሚታሰር መስሎን ነው አሉ። እኔም ህግ አለማወቅ ነው ያልኩት ለዛ ነው። መጨረሻ ግን ከተነገራቸው በኋላ አብረን ፎቶ እንነሳ ብለውኛል።

የተጫዋቾችህ ጠንካራ ጎን…?

“በአጭሩ ጠንካራ ጎናቸው ሀገራቸውን መውደዳቸው ነው። የሀገር ጉዳይ ስለሆነ ነው እንዲህ የተዋደቁት። ራሳቸውን ወይም ማንንም ስለሚወዱ አይደለም ሀገራቸውን ስለሚወዱ ነው ይህንን ውጤት ያመጡት። ከዚህም እየተነጋገሩ የሄዱት ይህንን ነበር። ለዛም ነው ዋንጫ ይዘው የመጡት።”

ስለነበረው የደስታ አገላለፅ?

“ደረቴን ስመታ ”እኔ ነኝ” ወይ የምትለው ብለውኛል። ግን እኔ እንደዛ አላልኩም። እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ነን ነው እያልኩ የነበረው። ውስጤ የነበረው ነገር ለማውጣት ነው። እኔ ተገፍቼ የመጣሁ ሰው ነኝ። ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖልኝ የመጣሁ ሰው አይደለሁም። ያመጡኝንም ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ። ግን እኔ አሁን አልነበረም ወደዚህ ብሔራዊ ቡድን የመጣሁት። ብቻ ፈጣሪ ፈቅዶ መጥቻለሁ። በድጋሜ አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና ሥራ-አስፈፃሚው አምነውብኝ ስላመጡኝ አመሰግናለሁ። ይህም ውስጤ ስላለ ነው። ብቻ ደስታ አገላለፄ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን በሚል ቢያዝ።”

ስለ ቀጣዩ የቦትስዋና ጨዋታ…?

“የቦትስዋናው ጨዋታ ቀን ወጥቷል። አሁን ተጫዋቾች በትን ተብዬ በትኛለሁ። መነጋገር ነበረንኝ ግን አሁን ተጫዋቾቹ ሄደዋል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ጠርቶ የሚያወራኝን ነገር እጠብቃለሁ። ካለው ነገር አንፃር ተጫዋቾቹ እዚሁ ተይዘው ቢሰሩ የተሻለ ይሆን ነበር ብዬ አስብ ነበር። እኔ ወደ ቡድኑ ከመጣሁ ጀምሮ አንድም የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጌ አላውቅም። ቢኖር ቡድኑ ተጠቃሚ ይሆን ነበር። ፌዴሬሽኑም በዚህ ላይ ይሰራል ብዬ አስባለሁ።”

ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር ስለሚኖር ግንኙነት

“እነ ናርዶስ፣ ብዙዓየሁ፣ ረድኤት እና መሳይ የመሳሰሉ ተጫዋቾች ዋናውም ጋር እኛም ጋር ያገለግላሉ። ባለው ነገር እየተስማማን እየተነጋገርን ነው ተጫዋቾቹን የምንጠቀምባቸው። ይህ ደግሞ በቀጣይም ይቀጥላል።”