የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጨረሻ ዝውውሩን አከናውኗል።
በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዓምና የሊጉን ዋንጫ ዳግም ማግኘቱ ይታወሳል። የሊጉ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የዞኑ የማጣሪያ ውድድር ላይ ተሳትፎ የፍፃሜ ተፋላሚ ሆኖ ተመልሷል። በኬንያ አስተናጋጅነት የተከናወነው ውድድር ከመጀመሩ በፊት የመዲና ዐወል፣ የምስራች ላቀው፣ ታሪኳ በርገና፣ ሀሳቤ ሙሳ፣ ትዝታ ኃይለሚካኤል እና ፀጋነሽ ወራናን ዝውውር አገባዶ የነበረው ክለቡም ከኬንያ መልስ እፀገነት ብዙነህ እና ትዕግስት ጌታቸውን ማስፈረሙን ዘግበን ነበር። አሁን ደግሞ የመጨረሻ ተጫዋቹን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉን ድረ-ገፃችን አውቃለች።
ባለንበት ሳምንት ክለቡን ለመቀላቀል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝታ ፊርማዋን ያኖረችው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቿ ዮርዳኖስ ምዑዝ ናት። የቀድሞ የደደቢት፣ ሲዳማ ቡና እና መቀለ 70 እንድርታ ተጫዋች የነበረችው ዮርዳኖስ ዓምና በአሠልጣኝ መሠረት ማኔ የሚመራውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተቀላቅላ ግልጋሎት ስትሰጥ ነበር። አሁን ደግሞ ባንክን ለማገልገል የሁለት ዓመት ፊርማ አኑራለች።