ፋሲል ከነማን ለቆ ለሦስት ዓመታት ለአልጄሪያው ክለብ ጄኤስ ካቢሌ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ለክለቡ የመጀመርያ ግቡን ካስቆጠረበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ስለተሰማው ስሜት እና ተያያዥ ሀሳቦች ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን አጋርቷል፡፡
በአሰልጣኝ አማር ሶሆያ የሚመራው ጄኤስ ካቢሌ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት የአልጄሪያ ሊግ 1 እረፍት ላይ ቢሆንም አቋሙን ለመፈተሽ እንዲሁም ለቀድሞው ፕሬዝዳንት መሐንድ ሸሪፍ ሀኔቺ አንደኛ ሙት ዓመት መታሰብያ ከዩኤስ ቢስካራ ጋር አድርጎ 5ለ0 አሸንፏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ጄኤስ ካቢሌ ኦ ሜዲያ ክለብን ከሜዳው ውጪ ገጥሞ ያለ ጎል ሲያጠናቅቅ የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን አድርጎ የነበረው ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም በዛሬው ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ ገብቶ ክለቡን ሙሉ ዘጠና ደቂቃ አገልግሏል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታን ጨምሮ በድምሩ ለክለቡ እስከ አሁን ሦስት ጨዋታዎችን ያደረገው ግዙፉ አጥቂ በ21ኛው ደቂቃ ላይ ለክለቡ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስለ አልጄሪያ ቆይታው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ከሀገሩ ውጪ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ የሚገኘው ሙጂብ “አልጄሪያ አልህምዱሊላህ ጥሩ ነው። ሀገሪቱን በደንብ እየተላመድኩ ነው፡፡ ቋንቋ ብቻ ነው እንጂ ችግሩ የማይለመድ ነገር የለም፤ ሁሉም ይለመዳል። አረብኛውንም እየሞካከርኩ ነው፤ እንግሊዝኛውንም እንደዛው” በማለት አዲሱ ኑሮውን እየለመደ መሆኑን ገልፆ ዛሬ ግብ በማስቆጠሩ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል። “የዛሬው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበር። ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጫውቻለሁ፤ ጎልም አስቆጥሪያለሁ። ባለው ነገር ደስተኛ ነኝ።”
ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የደመቀው አጥቂው ይህ ስኬቱን ለማስቀጠል አዲስ ፈተና ቢገጥመውም ለዚህ ዝግጁ መሆኑን ይናገራል። “ከሀገር ወጥቶ መጫወት ፈታኝ ነገር አለው። እንደዚህ እንደማወራልህ አይደለም። ራስህን ለሚገጥምህ ነገር ዝግጁ ማድረግ አለብህ። በተለይ በአዕምሮ በጣም ጠንካራ መሆን የግድ ይላል። እዚህ ከመጣው በኋላ ሊጋቸው ጠንካራ መሆኑን ተረድቻለሁ። ከእኛ ሊግ እጅግ የጠነከረ ነው፡፡ በተለይ ኃይል የቀላቀለ ፍጥነት የታከለበት ሊግ መሆኑን እየተመለከትኩ ነው። ዞሮ ዞሮ ከባድ ቢሆንም ራስህን ጠንካራ ካደረግክ ምንም የማይታለፍ ነገር የለም። እግርኳስ ሥራዬ ስለሆነ በየቀኑ መዘጋጀት እንዳለብኝ ይሰማኛል” ሲል ስለ ዝግጁነቱ ተናግሯል።
ሙጂብ በመጨረሻም “የአልጄርያን እግርኳስ የመጣሁ አካባቢ ትንሽ ለመላመድ ከብዶኝ ነበር። ይሄም የመጣው ከሀገር ወጥቼ ስጫወት የመጀመሪያዬም ስለሆነ ይመስለኛል። ግን ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ ቶሎ ነው የተላመድኩት። እንደ መጀመሪያው ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም፤ አሁን ላይ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ጎልም ማስቆጠር ጀምሪያለሁ” ብሏል፡፡