ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ከዚምባቡዌ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

የዓለም ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ከዚምባቡዌ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የማጣሪያውን ፍልሚያውን በሦስተኝነት አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጋና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ አስቻለው ታመነን በአህመድ ረሺድ እንዲሁም መስዑድ መሐመድን በሀይደር ሸረፋ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል። ጨዋታውንም በጥሩ ሁኔታ በመጀመር ገና በ5ኛው ደቂቃ መሪ ለመሆን ዚምባቡዌ የግብ ክልል ደርሰው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ዳዋ ሁቴሳ ወደ ሳጥን የላከውን የመሬት ለመሬት ኳስ ጌታነህ ከበደ አግኝቶት ከኋላው እየሮጠ ለነበረው ሽመልስ በኋላ እግሩ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ሽመልስ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ጌታነህ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት አቡበከር ናስር ሲያሻማው ምኞት ደበበ በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር።

በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠሩ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ባለሜዳዎቹ ዚምባቡዌዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ጨዋታውን ማድረግ ይዘዋል። ቀስ በቀስ ግን የኳስ ቁጥጥሩ ላይ እድገት እያሳዩ መጥተው በ29ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራቸውን አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘውን የመዓዘን ምት አምበሉ ቢሊያት ካሀማ አሻምቶት ተጨርፎ የደረሰው እና ራሱን በሩቁ ቋሚ ነፃ አድርጎ የቆመው ዋዲ ኢስማኤል እንደምንም ከኳሱ ጋር ቢገናኝም ሙከራውን ዒላማውን የጠበቀ ማድረግ ተስኖታል።

የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃዎች በጥሩ ብርታት የተጫወቱት የአሠልጣኝ ውበቱ ተጫዋቾች ቀጣዩን ሙከራ ለማድረግ ዚምባቡዌ የግብ ክልል የተገኙት በ34ኛው ደቂቃ ነበር። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዳዋም ከወደ ቀኝ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሮ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ደቂቃ በደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ዚምባቡዌ ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም አስቻለው ታመነን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው አህመድ ለግብ ዘቡ ተክለማርያም ለማቀበል የሞከረውን የኋልዮሽ አደጋ አምጪ ኳስ ግብ ጠባቂው የግብ ክልሉን ለቆ በመውጣት ለማፅዳት ሲሞክር ኳሱ ኩዳኩዋቺ ማሀቺ እግሩ ላይ ደርሶ ማሀቺ ከርቀት ወደ ግብነት ቀይሮታል። አጋማሹም ከርቀት በተቆጠረችው የማሀቺ ጎል በባለሜዳዎቹ መሪነት አድርጎ ተገባዷል።

የተከላካይ መስመራቸው ላይ ለውጥ በማድረግ (አስራት ቱንጆ ወጥቶ አስቻለው ታመነ ገባ) የሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ኢትዮጵያዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ማጥቃት ጀምረዋል። አጋማሹ በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃም በጥሩ ቅብብል የመጨረሻ ኳስ ከሀይደር የደረሰው ጌታነህ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ አግዳሚው መልሶበታል። ከዚህ አጋጣሚ በኋላም ቡድኑ ከምቸት ብሎ ዚምባቡዌ የሜዳ ክልል በመገኘት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥርም እጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ሙሉ ለሙሉ ተከላክለው መጫወት የቀጠሉትን ዚምናቡዌዎች ማስከፈት ተስኗቸዋል።

መሪ የሆኑት ዚምባቡዌዎች ምንም እንኳን ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው ለመጫወት ፍላጎት ቢያሳዩም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ሲታትሩ ታይቷል። በተለይ በ76ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በመገለዝ የሞከሩትን አስደንጋጭ ሙከራ ተክለማርያም አመከነው እንጂ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል የሚሆን ነበር።

ቢያንስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የማጥቃት ሀይላቸውን በተጫዋቾች ለውጥ ያሻሻሉት አሠልጣኝ ውበቱ በ86 ደቂቃ አቻ ሆነዋል። በዚህም የጌታነህን መውጣት ተከትሎ የመሐል አጥቂ ሆኖ መጫወት የጀመረው አቡበከር ናስር ተቀይሮ ከገባው መስፍን ታፈሠ የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ግብ ጠባቂውን በአስደናቂ ሁኔታ በማለፍ ግብ አድርጎታል። ይህች ጎል ለአቡበከር ናስር 2014 ከገባ ወዲህ የመጀመርያው ሆና ተመዝግባለታለች።

በቀሪ ደቂቃዎች ዋልያዎቹ አጥቅተው በመጫወት ወደ መሪነት ለመሸጋገር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ማለፍ እና አለማለፍ ላይ ምንም ተፅዕኖ የሌለው ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት መገባደዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምድቡን በ5 ነጥቦች በሦስተኝነት አጠናቋል። ዚምባቡዌ ደግሞ የምድቡ የመጨረሻ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።