ጋሞ ጨንቻ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስራ ስድስት ነባሮችን ኮንትራትም አራዝሟል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተካፋይ ከሆኑ ቡድኖች መካከል ካሉት የሊጉ ምድቦች በለ ስር የሚገኘው ጋሞ ጨንቻ ለ2014 የውድድር ዘመን ከወራት በፊት የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀምበሪቾ ዱራሜ አሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህን የቀጠረ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ሲያስፈርም አስራ ስድስት ነባር ውላቸውን የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ኮንትራት በአንፃሩ አራዝሟል፡፡ሶስት ወጣቶችን ደግሞ ከአካባቢው መልምሎ አሳድጓል፡፡
ትርታዬ ደመቀ ጋሞ ጨንቻን ተቀላቅሏል። በአርባምንጭ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና በ2013 የውድድር ዘመን እስከ አጋማሹ በጅማ አባጅፋር ቆይታ የነበረው አማካዩ የቀድሞው አሰልጣኙን ጥሪ ተቀብሎ ቡድኑን ተቀላቅሏል፡፡
የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ እና ስልጤ ወራቤ አማካይ አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ በወላይታ ድቻ ፣ ሀድያ ሆሳዕና ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ሺንሺቾ ግብ ጠባቂ የነበረው አስራት ሚሻሞ ፣ የአርባምንጭ ከተማ እና ሀምበሪቾ አጥቂ ብርሀኑ አዳሙ ከአዳዲስ ፈራሚዎች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን በረከት ተሾመ (ተከላካይ ከሶዶ ከተማ)፣ አስቻለው ኡታ (አጥቂ ከነቀምት ከተማ)፣ ማቲዮስ ኤልያስ (ከሀላባ አጥቂ)፣ በባህሉ ተስፋዬ (አጥቂ ከጎፋ ባራንቼ) እና አማኑኤል ተፈራ (ተከላካይ ከስልጤ ወራቤ) ክለቡን በአዲስ መልክ ተቀላቅለዋል።
ክለቡ ከአዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ ፋሲል ፋንታሁን፣ መኮንን አበራ እና ሲሳይ ዮሀንስ የተባሉ ወጣቶችን በምልመላ የስብስቡ አካል ሲያደርግ ነባር አስራ ስድስት ተጫዋቾች ክለቡ ኮንትራታቸውን ማደሱን ክለቡ ለድረገፃችን የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡