የሴካፋው ባለድሎች ዝግጅታቸውን በዚህ ሳምንት ይጀምራሉ

ከቀናት በፊት የሴካፋን ዋንጫን አንስተው በድል የተመለሱት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅታቸውን በቅርቡ ይጀምራሉ።

ለኮስታሪካው የ2022 ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያዎቹን ሁለቱን ጨዋታዎች አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሦስተኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ከቦትስዋና ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ ከኅዳር 23 – 25 ባለው ቀናት ከቦትስዋና ጋር የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድኑ ለዚህ የሚረዳውን ዝግጅት ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ አያት በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል በመከተም ልምምድ እንደሚጀምር ሰምተናል። ተጫዎቻቸው በዕረፍት የሚገኘቱ አሰልጣኝ ፍሬው ከነገ ጀምሮ ስብስባቸውን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ በሴካፋ ዋንጫ ከነበራቸው ስብስብ የተለየ ጥሪ እንደማያደርጉ እና ባለው ስብስብ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመልሱን ጨዋታ ከአስራ አምስት ቀን በኃላ በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል።