የመከላከያ ክስ ውድቅ ሆኗል

በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ከተማ የተረታው መከላከያ ያቀረበው የተጫዋች ተገቢነት ክስ ውድቅ ሆኖበታል።

አዲሶቹ አዳጊ ክለቦች መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ እሁድ ጥቅምት 21 በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ተገናኝተው እንደነበር ይታወሳል። ይህንን ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ 3-0 ቢያሸንፍም ከጨዋታው መገባደድ በኋላ ሦስት ነጥብ ያስረከበው መከላከያ “የተጫዋቾች ለውጥ ላይ ደንብ ተጥሷል” በሚል ክስ አቅርቦ ነበር።

በተለይም ክለቡ በጨዋታዎች ተጋጣሚ ክለቦች አምስት ተጫዋቾችን እንዲቀይሩ የሚፈቅደውን ነገርግን ከአምስቱ ተጫዋቾች መካከል ሦስቱ በአረንጓዴ ቴሴራ (ዋና ተጫዋቾች የተመዘገቡትን) ሁለቱ ደግሞ በቢጫ ቴሴራ እና ልዩ ቴሴራ የተመዘገቡትን ተጫዋቾች ብቻ እንደሆኑ የሚያትተውን ህግ አውስቶ ተጋጣሚው የነበረው አዲስ አበባ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ቀይሮ ያስገባቸው የሺዋስ በለው እና ምንተስኖት ዘካርያስ በቡድኑ ውስጥ በአረንጓዴ ቴሴራ የሚጫወቱ ናቸው በማለት ክስ አቅርቧል። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቾቹ ከተላለፈው ደንብ ውጭ የገቡ በመሆናቸው ተገቢ የሆነ ውሳኔ ይሰጠን በማለት ለሊጉ የበላይ ጨዋታው ከተጠናቀቀ ከሦስት ሰዓታት በኋላ ክስ ማስገባቱን ከቀናት በፊት ዘግበን ነበር።

የክለቡን ክስ ሲመለከት የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም የተጫዋቾቹን ምዝገባ በተመለከተ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማረጋገጫ ካስላከ በኋላ የሺዋስ በለው እና ምንተስኖት ዘካርያስ ከ23 ዓመት በታች ተመዝግበው ውል ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ ክሱ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፆ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።

መከላከያዎች ያቀረቡት ክስ በዛሬው ዕለት ውድቅ መሆኑን የሚያትት ደብዳቤ ከአክሲዮን ማኅበሩ ቢቀበሉም ይግባኝ ለማለት እንቅስቃሴ እንደጀመሩ ድረ-ገፃችን ተገንዝባለች።