የወላይታ ድቻ የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ ሆኗል

ለሁለት ዓመታት በክርክር የቆየው ጉዳይ በመጨረሻም የወላይታ ድቻን ይግባኝ ባለመቀበል ተጠናቋል።

በ2012 የውድድር ዘመን መጀመርያ በ2 ዓመት ውል ወልዲያን ለቆ ወደ ወላይታ ድቻ አምርቶ የነበረው ይግረማቸው ተስፋዬ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ መሰናበረቱን ተከትሎ ” ከመስከረም 2012 – ነሐሴ 2013 የሁለት ዓመት ኮንትራት እያለኝ ስድስት ወር ካገለገልኩ በኃላ ክለቡ አሰናብቶኛል። በመሆኑም የፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ፍትህ ይስጠኝ” በማለት ቅሬታውን አሰምቶ የዲሲፕሊን ኮሚቴውም ጉዳይን አይቶ ተጫዋቹ ያቀረበው ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ የኮንትራት ዘመኑ ይከበር በማለት ከዚህ ቀደም ውሳኔ አሳልፎ ነበር። በአንፃሩ ወላይታ ድቻ ”ተጫዋቹን ያሰናበትኩት በተደጋጋሚ ችሎታውን ሊያሻሽል ባለመቻሉ ደረጃ በደረጃ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የመጨረሻ ውሳኔ መደረሱን እና የዲሲፒሊን ኮሚቴው የወሰነው ውሳኔ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ሊያይልኝ ይገባል በማለት ጥያቄውን አቅርቧል።

በመጨረሻም የሁለቱንም አካላት ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት የመጨረሻ ውሳኔ ባወጣው ደብዳቤ የመጨረሻው ውሳኔ ተወስኗል። ወላይታ ድቻ ያቀረበው አቤቱታ በዲሲፒሊን ኮሚቴ የተፈጠረ ፍሬ ነገርም ሆነ የህግ ክፍተት የሌለ በመሆኑ በዲሲፒሊን ኮሚቴው ውሳኔ ፀንቷል። በውሳኔው መሠረት ወላይታ ድቻ ተጫዋች ይግረማቸው ተስፋዬ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ደሞዙ የሚከፍልም ይሆናል።