ከፍተኛ ሊግ | ቤንች ማጂ ቡና አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በአሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ እየተመራ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ቤንች ማጂ ቡና አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ አካቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስር ከሚገኙ አስራ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ቤንች ማጂ ቡና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ የቀድሞው የደሴ ከተማ አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙን መቅጠሩ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮውን የ2014 የውድድር ዘመንንም በአሰልጣኙ ይመራል፡፡ ከአንድ ወር በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ክለቡም አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ያስፈረመ ሲሆን አስራ ሁለት በክለቡ የነበሩ ነባር ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡ ልጅአለም ተሰማ የተባለ ወጣት ታዳጊንም ከክለቡ የታችኛው ቡድን አሳድጓል፡፡

ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ዳንኤል ኑዌር (ግብ ጠባቂ ከሻሸመኔ ከተማ)፣ ሀብታሙ ረጋሳ (አማካይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ)፣ ንጋቱ ጌዴቦ (ተከላካይ ከቡራዩ ከተማ)፣ ንጋቱ ፀጋዬ (ተከላካይ ከጋሞ ጨንቻ)፣ አንዋር መሐመድ (ተከላካይ ከደሴ ከተማ)፣ በረከት አድማሱ (ተከላካይ እና አማካይ ከደሴ ከተማ)፣ ቶስላች ሳይመን (አማካይ ከደሴ ከተማ)፣ ዘላለም በየነ (አጥቂ ከጋሞ ጨንቻ)፣ ሙሉጌታ ካሳሁን (አጥቂ ከዳሞት ከተማ)፣ አማኑኤል በቀለ (አጥቂ ከሮቤ ከተማ) እና ቴዎድሮስ ደበበ (አጥቂ ከሺንሺቾ ከተማ) ናቸው፡፡

ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው የወዳጅነት ጨዋታዎችን እያደረገ አቋሙን እየፈተሸ የሚገኝ ሲሆን በያዝነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ የዋናው ቡድን ጋር በቢሾፍቱ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዙም ጭሞር ነግረውናል፡፡