ከወራቶች በፊት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሎ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምስት ወጣቶችን ጨምሮ በድምሩ አስራ አንድ ተጨማሪ ተጫዋቾች አስፈርሟል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዲቪዚዮን ተካፋይ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወራቶች በፊት የአሰልጣኝ መሠረት ማኒን ውል ካራዘመ በኋላ ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ ከሰሞኑ ለ2014 የውድድር ዘመን ዝግጅቱን የጀመረው ክለቡ አምስት ወጣቶችን ጨምሮ በድምሩ አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል የአዳዲሶችን ቁጥር ሀያ አድርሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ረዘም ላሉ ዓመታት ቆይታን ያደረገችው እና በያዝነው አመት መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ ከክለቧ ባንክ ጋር ተሳትፎ የነበራት የመስመር አጥቂዋ ብዙነሽ ሲሳይ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምርታለች፡፡ በወሊድ ምክንያት ከእግር ኳሱ ጠፋ ያለቺው የአንጋፋዋ አጥቂ ሽታዬ ሲሳይ ታናሽ እህት የሆነችው ብዙነሽ በብሔራዊ ቡድንም ከዚህ ቀደም ግልጋሎት ሰጥታለች።
ዙለይካ ጁሀድም ማረፊያዋ ኤሌክትሪክ ሆኗል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስደናቂ አቋምን በማሳየት የምትታወቀዋ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ አቃቂ ቃሊቲን በመልቀቅ ለኤሌክትሪክ ስትፈርም የቀድሞዋ የሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ባለፈው ዓመት በመከላከያ ቆይታን ማድረግ የቻለችው አጥቂዋ አይዳ ዑስማንም ክለቡን ተቀላቅላለች።
ገነት ኤርሚያስ (ግብ ጠባቂ ከሀዋሳ ከተማ)፣ ገነት አንተነህ (ግብ ጠባቂ ከአቃቂ ቃሊቲ) ዕድላዊት ተመስገን (አጥቂ ከድሬዳዋ ከተማ) ወደ ስብስቡ የተቀላቀሉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜላት ገዛኸኝ (አማካይ) ፣ መሰረተ ፈረደ ( አማካይ) ፣ ዮርዳኖስ ታሪኩ (አማካይ) ፣ ቢሊየን ሲሳይ (አማካይ) እና ልደት ታዲዮስ (አጥቂ) ክለቡን የተቀላቀሉ ወጣት ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡