አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ዘለግ ያለ መግለጫ ሰጥተዋል

👉”አሁን ባለው ሁኔታ ጌታነህ በዛ ቦታ የመጀመሪያ ተመራጭ ነው…”

👉”እንደ አጋጣሚ የብዙ ነገር መሞከሪያ ቡድን የሆነው ይህ ቡድን ነው…”

👉”ያሉን ግብ ጠባቂዎች መጠበቁ ነው እንጂ የሚያዋጣው መኮርኮሙ አያስኬደንም…”

👉”ሁለት ነገር አስበን ነበር ወደ ጨዋታዎቹ የሄድነው…”

ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5 ነጥቦችን በማግኘት ወደ ዓለም ዋንጫ ሳያልፍ ቀርቶ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ እና እሁድ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ያደረገውን ቡድን ተንተርሶም የብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለአንድ ሰዓት ከአስር ደቂቃዎች የቆየ መግለጫ ዛሬ ከሰዓት ከ9 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሰጥተዋል።

የቡድኑ አሠልጣኝም በቅድሚያ ጨዋታዎቹን ተንተርሰው ተከታዩን ሀሳብ በመስጠት ንግግራቸውን ጀምረዋል። “ወደ ጨዋታዎቹ ከመሄዳችን በፊት ከተጫዋቾች ጋር ተያይዞ መጠነኛ አለመሟላቶች ነበሩ። 23 ተጫዋቾችን ይዘን ለመሄድ ሁሉን ነገር ጨርሰን ልንሄድ ስንል ሽመክት ጉግሳ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ቀርቶ 22 ተጫዋቾችን ይዘን ለመሄድ ተገደናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ኤርፖርት ላይ ደግሞ መናፍ ዐወል መጠነኛ ህመም አጋጥሞት በረራችን ለ1 ሰዓት መስተጓጎል አጋጥሞን ነበር።

“በጨዋታዎቹ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመን ጠብቀም ነበር። ይህ ቢሆንም ሁለት ነገር አስበን ነበር ወደ ጨዋታዎቹ የሄድነው። አንደኛው ከአፍሪካ ዋንጫው በፊት ስለሆነ ተጫዋቾቹ የጨዋታ ልምድ የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር ነው። ሁለት ደግሞ ውጤቱ ከክብር በዘለለ እኛ ላይ የሚፈጥረው ነገር ባይኖርም ፍትሀዊ መሆንን በመከተል ማንምን ለመጥቀም ማንንም ለመጉዳት ባለማሰብ ለመጫወት በመጣር ጨዋታውን ቀርበናል። በእቅዳችን መሠረት ከሜዳችን ውጪ ከጋና ጋር አቻ መውጣታችን ለእኛ ጥሩ ነገር ነው። ለእኛ ራሳችንን ለማየት ብንጠቀምበትም ጋናዎች ግን ጨዋታው ያስፈልጋቸው ነበር። ጨዋታውም ላይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የታየው ነገር ይህ ነው። ይህንን ተቋቁመን ብንሄድም በቅጣት ምት ጎል አስተናግደናል። የጨዋታውን አብዛኛውን ጊዜ ግን ብልጫ ለመውሰድ ሞክረናል። ወደ ጋና ሄደን ከተጫወትነው ጨዋታም በተሻለ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረን ተጫውተናል። ይህ ለእኛ ትልቅ እድገት ነው። በጨዋታዎቹ ከዚህ በፊት በራሳችን ሜዳ ኳስን ከማንሸራሸር በበለጠ ወደ ሰው ሜዳ ሄደን የተጫወትንበት ነበር።” በማለት ከጉዞ እና ከጋና ጋር የተደረገውን ጨዋታ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አስከትለው ደግሞ ወደ ሀራሪ አቅንተው ዚምባቡዌን የተፋለሙበትን ጨዋታ በማንሳት ሀሳባቸውን ቀጥለዋል።

“ሌላው ከሦስት ቀን በኋላ ያደረግነው ጨዋታ ነው። እነሱ (ዚምባቡዌዎች) በቅድመ ጨዋታ አስተያየት ላይ ኢትዮጵያን በሰፋ ጎል ማሸነፍ እንዳሰቡ ሲናገሩ ስንሰማ ነበር። ግን እኛ በጨዋታው የተሻለ ለመጫወት ጥረናል። ጨዋታው ከመጀመሩ ከአራት ሰዓታት በፊት አስቻለው ታመነ ከሁለት ቢጫ ጋር ተያይዞ ማሰለፍ እንደማንችል አወቅን። እንደነገርኳችሁ ደግሞ በዛ ቦታ መናፍ ብቻ ነበር የነበረን። እሱም በገለፅኩት መልኩ የጤና እክል ስለነበረበት አልተጠቀምንበትም። እርግጥ መናፍ በጤናው ላይ መሻሻል ቢያሳይም ለጨዋታ ዝግጁ አልነበረም። ይህንን ተከትሎ በኢንተርናሽናል ጨዋታ በዛ ቦታ ብዙ ልምድ የሌለውን አህመድ ለመጠቀም ተገደናል። የመጫወቻ ፎርሙን ከላክን በኋላ ፊፋ አስቻለውን መጠቀም እንደምንችል አሳወቀን። ግን ተመልሰን አስቻለውን ለማሰለፍ ጊዜም ስላለነበረ ባለን ለመጠቀም ሞክረናል።

“ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን መጠን እና ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደመጫወታችን እንዲሁም ከጨዋታ ሰዓቱ አንፃር ትንሽ ከበድ ይል ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በጥሩ ሁኔታ ሄደን ነበር። ግን በቀላል ስህተት ጎል አስተናግደን መመራት ጀምረናል። ይህ ቢሆንም በአቡበከር አማካኝነት ጎል አግብተን አቻ ወተናል። ከጋናም ሆነ ከዚምባቡዌ ጋር ከሜዳችን ውጪ አቻ መውጣታችን ለእኛ ትልቅ የሥነ-ልቦና ስንቅ ይሰጠናል። ከምንም በላይ ጨዋታዎቹን ከዚህ በፊት የመጫወት ዕድል ብዙ ያላገኙ ተጫዋቾችን ለማየት ተጠቅመንበታል። በዚህም የተጫዋች አማራጮቻችንን አይተንበታል።” በማለት ሁለቱን ጨዋታዎች ተንተርሶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከአሠልጣኙ ገለፃ በኋላ ደግሞ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምልሾች መሰጠት ተጀምረዋል።

በጋና እና በዚምባቡዌ ጨዋታ ላይ ስለነበረው የጨዋታ አቀራረብ?

ከሁለቱ ቡድኖች ጋር የነበረን አቀራረብ በተወሰነ መልኩ መቀራረብ ነበረው። ግን ትንሽ ልዩነትም አለው። ከጋና ጋር ስንጫወት በጣም ደፍረን ተጫውተናል ብዬ መናገር አልችልም። ወደ ራሳችን የግብ ክልልም ተጠግተን አልተጫወትንም። ትንሽ ወደ ማሐል ተጠግተን ነበር ስንጫወት የነበረው። ከዚምባቡዌ ጋር ግን በዚህ መልኩ አልተጫወትንም። ትንሽ ደፈር ብለን ለመንቀሳቀስ ጥረናል። ይህ ቢሆንም የሚያስፈራን ነገር ነበር። በጣም የሚያጠቃ ቡድን ለመገንባት ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ድረሰ ያሉ ተጫዋቾች መናበብ አለባቸው። የነበረን እቅድ አህመድን በአስራት ቦታ አሰልፈን መጠነኛ የጤና እክል የነበረውን አስራት ማሳረፍ ነበር። ከዛ አስቻለውን እና ምኞትን በመሐል ተከላካይነት መጠቀም። ግን በአስቻለው ምክንያት ይህ አልሆነም። ከዚህ መነሻነት አብረው ያልተጫወቱትን ምኞት እና አህመድን ለመጠቀም ተገደናል። ይህ ደግሞ ትልቅ የመዋቅር ጥያቄ ነው።

ቡድኑ ኳስ ሲመሰርት ስላለበት ቀርፋፋነት?

እኛ ገና ጀማሪዎች ነን። መፍጠን በሚያስፈልገን ቦታዎች ላይ መፍጠን እንዳለብን እረዳለሁ። በዚህ ውድድር የቀላቀልናቸውን ተጫዋቾች ስድስት ቀን ብቻ ነው ያገኘናቸው። ይህ በጣም አጭር ነው። በዚህ አጭር ቀን ሁሉንም ነገር ተጫዋቾች ላይ ማስረፅ ከባድ ነው።

ከመጫወቻ ሜዳ ጋር ተያይዞ ስላሉ ልዩነቶች?

ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ወድቀው በዚህ ደረጃ የሚጎዱት እኛ ሊግ ላይ ብቻ ነው። እውነት ለመናገር የተሻለ ሜዳ ማግኘታችን ሊጠቅመን ይችላል። ግን እዚህ ያሉት ተጫዋቾች የሚጫወቱት ባለን ሜዳ ነው። ሜዳው አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን እንኳን አቅም የሌላቸው ነው የሚያስመስለው። ግን በመልካም ሜዳ ላይ ከመጫወት ወደ አስቸጋሪ ሜዳ መምጣት በጣም ከባድ ነው። ለእኛም ቢሆን ግን ከዚህ ወደ ዛኛው መሄድ ከባድ ነው። ከዛኛው ግን አይበልጥም።

በማጣሪያው ቡድኑ ስለነበረው ዕቅድ?

በውጤት ደረጃ መናገር አያስፈልግም። በጊዜ ነው የወጣነው። ግን ብዙ ጥቅሞችን አግኝተን ነው ከውድድሩ የወጣነው። ቢያንስ ቢያንስ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በቀን በቀን ተስፋ የሚያስቆርጥ ውጤት እንዳያጋጥመን ጥረናል። ይህ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው።

ዳዋ ሆቴሳ ስላሳየው ብቃት?

ዳዋ ጥሩ እንደተጫወተ አይተናል። ማድረግ የምንፈልገውን አብዛኛውን እያደረገ ነበር። እኛ የምንጫወትበትን መንገድ ለመረዳት ግን ትንሽ ጊዜ ይፈልጋል። ወደፊት ጥሩ እየተጫወተ በቀጠለ ቁጥር ሌላ አማራጭ የሚሰጠን ተጫዋች ስለሆነ እንጠቀምበታል።

ጌታነህ እና አቡበከር ላይ ስለሚነሱ ሀሳቦች?

አሁን ባለው ሁኔታ ጌታነህ በዛ ቦታ የመጀመሪያ ተመራጭ ነው። በአግባቡም ቡድኑን በአምበልነት እና በኃላፊነት እየረዳን ነው። ከኳስ ውጪም ከኳስ ጋር እየጠቀመን ነው። ጎሎችንም እያገባ ነው። ይህንን ሀሳብ ከእሱም ሆነ ከአቡበከር ጋር እናወራለን። አቡበከር ገና ነው። ገና ብዙ የሚጠበቅበት ነው። ካሳለፈው ይልቅ ወደፊት የሚያሳልፈው ትልቅ ነው። የአሁኑንም ጎል አቡበከር ያገባው በሀፍ ስፔሰስ ቦታ ተገኝቶ ነው። በ9 ቁጥር ቦታ አቤል ነበር። የመስመር ተጫዋቾች እንደ መስመር ዳኛ መስመሯን ታከው ብቻ እንዲሮጡ አናደርግም። አቡበከር እዛ ቦታ ተጫወተ ማለት ክሮስ አድራጊ ነው ማለት አይደለም።

ቡድኑ ላይ ስላለሉ ችግሮች እና ስህተቶች?

የተናጥልም ሆነ ቡድናዊ ችግሮች ነበሩ። የግል ስል ማንምም ተጠያቂ ማድረግ ፈልጌ አይደለም። ይህ እግርኳስ ነው። እንደ ቡድንም የነበሩብን የተለያዩ ችግሮች ነበሩ። ይህንን ችግር ለማስተካከል እንጥራለን። ከተቆጠሩብን 7 ጎሎች 2ቱ ብቻ ናቸው ቡድናዊ ስህተት። ሌሎቹ በጥቃቅን ስህተቶች የተገኙ ናቸው። እነዚህ ስህተቶች መቼ ይቀረፋሉ የሚለውን የሚመልሰው ልምድ ነው። ከባዱ አጠቃላይ እንደ ቡድን የተዋቀርንበት ነገር ቢፈርስ ነበር።

ለአፍሪካ ዋንጫው ስለሚኖር ዝግጅት?

ለአፍሪካ ዋንጫው የሚኖረን 15 ቀን ነው። የጉዞ እና ተለያዩ ነገሮችን ስትቀናንስ 12 ምናምን ቀን ይሆናል። እየጠራን ያለነው ከዚሁ ሊግ ነው። እነዚህን ተጫዋቾች በዛ ጊዜ ጠርቶ የምናስበውን ማስረፅ ከባድ ነው። ምናልባት ግን ሌላ ዓይነት የመዘጋጃ ጊዜ እንዲኖር ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገርን ነው። ከጨዋታው በፊት 2 ወይም 3 የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማግኘትም እየተሰራበት ነው።

የአፍሪካ ዋንጫ የዝግጅት ጊዜ ማጠር?

እንደ አጋጣሚ የብዙ ነገር መሞከሪያ ቡድን የሆነው ይህ ቡድን ነው። በዝግ ስታዲየም መጫወት፣ ከሜዳ ውጪ የተጫወተ እና አጭር ቀን የሚዘጋጀው ቡድን ነው ይህ ቡድን። ክረምት በሆነበት ጊዜ ላይ ለ1 ወርም ተጫዋቾቹን አግኝተናል። ውድድር ውስጥ ሆነው ግን ትልቁ 12 ቀን የተዘጋጀነው። ተጫዋቾች እኛ ጋር መጥተው የተለየ የአካል ብቃት ሥራ አይሰሩም። በመጠኑም ቢሆን ግን የመጠበቅ ነገር እኛም እናሰራለን። ከአማካይ ክብደት በላይ (ኦቨር ዌት) እና ከአማካይ ክብደት በታች (አንደር ዌት) ከመሆን ጋር ተያይዞ እየሰራን ያለነውም ነገር አለ። ብቻ ባለን ጊዜ እንሰራለን። ከውድድሩ በፊት ሦስት ወይም ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ እየሰራን ነው።

ስለጌም ሞዴል…?

የኢትዮጵያ ብሔራዉ ቡድን የጨዋታ መንገድ ይሄ ነው ተብሎ የተቀመጠ ነገር ከመምጣቴ በፊት አላገኘሁም። ይህንን ተከትሎ ከዕድሜ እርከን ቡድኖች ጀምሮ የመጣ ነገር የለም። ይህ ማለት የቀደሙት አሠልጣኞች የራሳቸው የጨዋታ መንገድ የላቸውም ማለት አይደለም። እኛ የምንጫወትበትን መንገድ እና እንቅስቃሴ፣ የምልመላ እንዲሁም የልምምድ ሁኔታዎችን የሚያቅፍ ነገር እንዲኖረን እየሰራን ነው። በዛም ነው እየሰራን ያለነው።

የግብ ጠባቂ ጉዳይ…?

ተክለማርያም እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቀላል ጎል ገብቶበታል። ያ ኳስ አምሮ ላይ የፈጠረው ነገር አለ። ጎሉ ለምን ገባ ሳይሆን በዛ መልኩ መግባቱ ስነ ልቦናውን ትንሽ ረብሿል። ቡድኑንም ጎድቻለው የሚል ሀሳብ ነበረው። ይህንን ተረድተናል። በሁለቱ ጨዋታ ደግሞ ፋሲልም ስለሌለ እሱንም አውርተነው አስገብተነዋል። ሲጀምር የጋናው ጨዋታ (ሁለተኛው) ትልቅ ኃላፊነት ነበረው። ጫናም ነበረው። በዚህ ጫና ውስጥም ከትልቅ ግብ ጠባቂ የሚጠበቅ ደብል ሴቭ ገና በጊዜ አድርጓል። ይህ የእሱንም የቡድኑንም ስነ ልቦና ያሳደገ ነው። ጥሩ ተጫውቷል። ያሉን ግብ ጠባቂዎች መጠበቁ ነው እንጂ የሚያዋጣው መኮርኮሙ አያስኬደንም። አጋጣሚ ሆኖ ከጋና ጋር ተሰልፎ ያንን የመሰለ ብቃት ማሳየቱ ለእሱ ያለንን ነገር የሚጨምር ነው።