የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዕጣ ማውጣት መርሐግብር ለቀናት ተራዝሟል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ እና የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር የዕጣ ማውጫው ቀን ለቀናቶች ተገፍቷል፡፡

የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ እና የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች የሚጀመሩበትን እና ዕጣ የሚወጣባቸውን ቀኖች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሴቶች ልማት እና ዳይሬክቶሬት ኮሚቴ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አስራ ሦስት ክለቦችን አካቶ የሚደረገው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር የሚጀመርበት ቀን ታኅሳስ 17 ሆኖ የሚዘልቅ ሲሆን የዕጣ ማውጣቱ ቀን ባለፈው ማክሰኞ ኅዳር 7 የሚደረግ የነበረ ቢሆንም የቀን ለውጥ በማስፈለጉ በያዝነው ወር ኅዳር 17 የዕጣ ማውጣት እና የደንብ ውይይቱ እንዲደረግ የቀን ሽግሽግ ተደርጎበታል፡፡

በአንፃሩ አስራ ስድስት ክለቦችን ያሳትፋል ተብሎ የሚጠበቀው የሁለተኛው ዲቪዚዮን ውድድር የዕጣ ማውጣቱ ቀን ኅዳር 8 የነበረ ቢሆንም የቀን ለውጥ ተደርጎበት እንደ አንደኛ ዲቪዚዮኑ ሁሉ በተመሳሳይ ቀን ኅዳር 17 የዕጣ ማውጣት እና የደንብ ውይይቱ የሚደረግበት ቀን ሆኖ ተቆርጦለታል፡፡

በርካታ ክለቦች ከምዝገባ ጋር በተያያዘ በቀነ ገደቡ መሠረት እየተመዘገቡ አለመሆኑን ተከትሎ የቀን መግፋቱ እንደተከሰተ የሰማን ሲሆን በተለይ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ላይ የሚታየው የበጀት ክፍተት ለዚህ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ በዚህ ዲቪዚዮን ላይ ከሚወዳደሩ ክለበች መካከል የሻሸመኔ ከተማ እና የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በበጀት ምክንያት በውድድሩ ላይ ተካፋይ እንደማይሆኑ ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ የቻለች ሲሆን ክለቦች ለውድድር የሚመዘገቡበት ዕለትም ኅዳር 30 የመጨረሻው ሆኖ አቅጣጫ በልማት ኮሚቴው ተቀምጧል፡፡