የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ጀምሯል

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ 22 ተጫዋቾችን የጠራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት ለወሳኙ ጨዋታ ዝግጅቱን ጀምሯል።

በቀጣይ ዓመት በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመካፈል የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የሩዋንዳ አቻውን በደርሶ መልስ ውጤት በሰፋ የግብ ልዩነት ካሸነፈ በኋላ በሦስተኛ ዙር ጨዋታ ከቦትስዋና ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ከቀናት በኋላ ማድረግ ይጀምራል። ለዚህ ጨዋታ ከትናንት በስትያ ለ22 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረቡት አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤልም በዛሬው ዕለት ቡድኑን ልምምድ ማሰራት ጀምረዋል።

ትናንት 7 ሰዓት ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልዕቀት ማዕከል ሪፖርት ያደረጉት ተጫዋቾችም በተሟላ ሁኔታ ዛሬ ጠዋት ከ3 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው ልምምድ ላይ ተሳትፈዋል። እጅግ ለልምምድ ምቹ ባልሆነው ሜዳ ላይ በተከናወነው ልምምድ ላይም አሠልጣኙ ቀለል ያሉ የትንፋሽ እና የማላቀቅ ይዘት ያላቸው የሩጫ እና የማፍታታት ሥራዎችን አሰርተዋል። ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ከተከናወነው የትንፋሽ ልምምድ በኋላ ደግሞ ተጫዋቾች ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ እንዲያፍታቱ ተደርጎ 4 ሰዓት ሲል ልምምዱ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ቡድኑን በአዲስ መልክ የተቀላቀሉት (በሴካፋ ውድድር ላይ ያልነበሩ) ገነት ኃይሉ ፣ ዮርዳኖስ ምዑዝ፣ ንግስት አስረስ እና ቤተልሄም ታምሩን ጨምሮ በሴካፋ የነበረችው መስከረም ኢሳይያስ የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች ከቡድኑ ጋር ልምምድ ከሰሩ በኋላ ከኳስ ጋር የነበረው የማፍታታት ሥራ ሲከወን ተነጥለው ለብቻቸው ሜዳውም ሲዞሩ አስተውለናል። ወደ ሴካፋ እንዲያመራ በታሰበው ነገርግን ከጨዋታ መደራረብ ጋር ተይይዞ እረፍት ተሰጥቷት የነበረችው እና በአሁኑ ስብስብ ውስጥ የተካተተቸው አረጋሽ ግን ከአጋሮቿ ጋር ሙሉ ልምምድ ሰርታለች። ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ በተመለከተችው መሠረት ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ውስጥ የነበሩት የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ቅጣው ሙሉ ግን በስፍራው አላየናቸውም።

ከኅዳር 23-25 ባሉት ቀናት ከሜዳው ውጪ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ቡድኑን ዛሬን ጨምሮ ቀጣዮቹን ውስን ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን እየሰራ እንደሚቀጥል ታውቋል። ምንም እንኳን ቡድኑ ማረፊያውን በካፍ የልዕቀት ማዕከል ቢያደርግም የመለማመጃ ሜዳው ምቹ ካለመሆኑ መነሻነት የልምምድ ሥፍራውን ሊቀይር እንደሚችል ሰምተናል።

ያጋሩ