ሊጉን እየመሩ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ከጉዳት ሁለት ተጫዋቾችን ሲያገኙ የሌሎች ሁለት ተጫዋቾችን ግልጋሎት በአንፃሩ አሁንም አያገኙም፡፡
የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመራ የ2014 የውድድር ዘመን አጀማመሩን አሳምሯል፡፡ ሊጉ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች እስኪቋረጡ ድረስ በተደረጉ የሦስት ሳምንት የሊጉ መርሀግብሮች ያደረገው ክለቡ ሁሉንም ድል በማድረግ በሰበሰበው ዘጠኝ ነጥቦች ሊጉን እየመራ ይገኛል፡፡ ከሀያ ቀናት መቋረጥ በኋላ የፊታችን ዕሁድ በአራተኛ ሳምንቱ ፕሪምየር ሊጉ ሲመለስ ዐፄዎቹ ዕለተ ሰኞ ቀን 9፡00 ላይ አዲስ አበባ ከተማን በመግጠም ወደ ውድድር ሲመለስ ሁለት ተጫዋቾችን ከጉዳት መልስ የሚያገኝ ይሆናል፡፡
በሦስተኛ ሳምንት ጨዋታ ቡድኑ ጅማ አባጅፋርን ሲረታ ጉዳት ገጥሞት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣው እና ከብሔራዊ ቡድኑሞ ውጪ ሆኖ የነበረው ተከላካካዩ እና አምበሉ ያሬድ ባዬ እና በተመሳሳይ አማካዩ ይሁን እንዳሻው ከጉዳት ተመልሰው መደበኛ ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ ጨወታ ከወልቂጤ ጋር ፋሲል ሲጫወት ጉዳት ገጥሞት የሦስተኛውን ሳምንት ጨምሮ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ውጪ ሆኖ የሰነበተው አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው በእግሩ ላይ ከገጠመው ጉዳቱ እስከ አሁን ማገገም ያልቻለ ሲሆን በተጨማሪነትም የጥርስ ህክምና ላይ ስለሚገኝ ላልተገለፁ የሊጉ የጨዋታ ሳምንታት ከሜዳ መራቁ ዕርግጠሸ ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢም አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ከክለቡ ስብስብ ውጪ መሆኑን ተረድተናል፡፡