በሲዳማ ክልል የወጣው የሰዓት እላፊ ገደብ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖ ይኖረው ይሆን?

የዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ ጅማሬውን በማድረግ እየተከናወነ ሲገኝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያትም ለቀናት እረፍት ወስዶ ቆይቷል። ፋሲል ከነማን መሪ ያደረገው ሊጉም ከሦስት ቀናት በኋላ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ማድረግ ይቀጥላል።

ይህ በእንዲህ እንዳላ ውድድሩ እየተከናወነበት የሚገኘው የሲዳማ ክልል ኮማንድ ፖስት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የሰአት እላፊ እና የእንቅስቃሴዎች ገደብ እንዲሁም ክልከላዎችን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የጨዋታዎች ሰዓት ላይ ለውጥ ይኖር ይሆን ብለን የሊጉን የበላይ አካል ጠይቀናል።

በዋናነት በተቀመጠው የሰዓት እና የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪ ሞተር ሳይክል አንድ ሰው ብቻ ጭኖ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት፣ የህዝብ ትራንስፖርት እና ታክሲዎች ደግሞ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ይፋ ሆኗል። አክሲዮን ማኅበሩ እና የውድድሩ የቀጥታ ሥርጭት መብት ያለው ዲ ኤስ ቲቪ ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድ የሚደረጉ ጨዋታዎች 8 እና 12 እንዲሁም በአዘቦት ቀን (ከሰኞ እስከ ዓርብ) የሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ 9 እና 12 ሰዓት እንደሚደረጉ ቀድመው ይፋ አድርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በጨዋታዎቹ ውስን ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ሜዳ እንዲገኙም መደረጉ ይታወቃል። ታዲያ ይህ ከሆነ እና የጨዋታ ቀን ሁለተኛ ጨዋታዎች ከ12 ሰዓት ጀምሮ የሚደረጉ ከሆነ መገባደጃቸው ለ2 ሰዓት መጠጊያ ሰዓት ላይ ይሆናል። በዚህ አካሄድ ከቀጠለ ደግሞ ከ2 ሰዓት በኋላ የህዝብ መጓጓዧ አማራጮች አገልግሎት ስለማይሰጡ ደጋፊዎች እንዴት ይሆናሉ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ሆኗል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአክሲዮን ማኅበሩ የፀጥታ ጉዳዮች ዋና ተወካይ አቶ ሀብታሙ ዛሬ ወደ ሀዋሳ በማቅናት መጥራት ያለባቸው ጉዳዮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደተወያዩ አውቀናል። ውይይቱን ተከትሎ ባለድርሻ አካላቶቹ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዳይገቡ ክልከላ እንዳላደረጉ የተረዳን ሲሆን የጨዋታ ሰዓቶቹ ላይም ለውጦች እንደማይኖሩ ተነግሮናል። ይህንን ተከትሎ በክልሉ የወጣውን ክልከላ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መግባት እንደሚችሉም ተገልጿል።

ከሊጉ ጅማሮ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና እስከ ሦስተኛ ሳምንት ድረስ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶችን ሽያጭ ሲያቀርብ የነበረው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር ከአራተኛ ሳምንት ጀምሮ የጨዋታ ቀን ትኬቶችን ባለሜዳ ቡድኖች እንዲቆጣጠሩት እንደሚያደርግ ተሰምቷል።